Thursday, September 25, 2014



         

               መስቀል
መስቀል ማለት የተመሳቀለ ማለት ሲሆን መስቀያ፣መሰቀያ ፤ማሰቃያ የሚል ተያያዥ ትርጉሞችን ይሰጣል ፡፡
           ጥንታዊያን ነገስታት የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውን ወንጀለኞችና ህግ ተላላፊዎችን በተለያየ መንገድ እንዲገደሉ ያደርጉ ነበር፡፡ ለምሳሌ ባቢሎናውያን ሰዎችን እሳት በሚነድበት ጉድጓድ እየጨመሩ አሰቃይተው ሲገሉ ዳን 31-30 ፋርስና ሚዶኖች ደግሞ አናብስት ወደ ታሰሩበት ጉድጓድ ወንጀለኛውን በመመርመር ተሰባብሮ እንደሞተና ለአውሬ እራት እንዲሆን ያደርጋሉ ዳን 6÷1–28 አረቦች በሰይፍ በመቅላት ሲያስወግዱ አይሁዶች ደግሞ በድንጋይ በመውገር ይገድላሉ፡፡ ዘዳ21÷21 ዮሐ.8÷1-11 ኢያ.10÷26
     በጥንት ዘመን ከነበሩት ገናና መንግስታት አንድ የሆነውና ዓለም በታሪክ ከተመለከተቻቸው ታላላቅ ኢምፓየሮች ግንባር ቀደም የሆነው የሮማ ኢፓየር ደግሞ በህግ የተፈረደባቸውን ወንጀለኞች በእንጨት መስቀል በመስቀል እንዲሞቱ ያደርግ ነበር፡፡ በመሆኑ ጌታችን ኢየሱስ በእንጨት መስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት የተፈረደበት በአይሁድ ህግ ሳይሆን የጊዜው የመላዋ እስራኤል ገዥ በነበሩት ሮማውያን ወንጀለኛን በሚገሉበት መንገድ ነው ፡፡
     ከክርስቶስ ልደት በፊት አምስት ዓመት ቀደም ብሎ በይሁዳ ብቻ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች በመስቀል ተሰቅለው እንዲሞቱ እንደተደረገ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ ፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላ 60. አካባቢ እንኳን ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች በመስቀል ተሰቅለው ተገድለዋል ፡፡
     ክርስቶስ በተሰቀለበት ዘመን አራት አይነት የመስቀያ አይነቶች ነበሩ፡-
1.     2.      3. x    4.   1                                                                           ክርስቶስ  የተሰቀለው ግን በመጀመሪያው ወይም የመደመር ምልክት በሚመስለው ነው ፡፡
በጊዜው ሰው በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት ሲፈረድበት ባብዛኛው የሚከተሉት ነገሮች ይፈፀማሉ -
1.   የሚሰቀል ከሆነ አይገረፍም በክርስቶስ ላይ ግን ሁለቱም ተፈፅመዋል ማቴ. 27÷26
2.   የመሰቀያ መስቀሉን እንዲሸከም ይደረጋል ዮሐ.19÷17
3.   ከከተማ ውጭ እንዲወጣ ይደረጋል፤ ዮሐ.19÷20
4.   በምስማር ተቸንክሮ ወይም በገመድ ታስሮ እንዲሞት ይደረጋል ፡፡ ክርስቶስን በገመድ እጆቹ መጋጠሚያ ላይ ካሰሩት በኋላ በምስማር መዳፉንና እግሮቹን ቸንክረውታል፡፡
5.   በመስቀሉ ጫፍ ላይ የተሰቀለበት ምክንያትና የፈጸመው መንጀል ይፃፋል፤ ኢየሱስን ለሞት የሐሰት ክስ የአይሁድ ንጉስ ነኝ ብሎ ቄሳርን ተቃውሟል የሚል ስለ ነበር ... ( ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሰ አይሁድ) የናዝሬቱ ኢየሱስ የአይሀድ ንጉስ የሚል የስላቅ ጽሁፍ በመስቀሉ አናት ላይ በላቲን በግሪክ በዕብራይስጥ ቋንቋ ጽፈው ሰቅለው ነበር ዮሐ.19÷19 ቆላ. 2÷14-15
6.   የስቃይ ማደንዘዥ መጠጥም ለሚሰቅሉት ይሰጥ ነበር፤ የስቃይ መጠጡን በኢየሩሳሌም የነበረው የሴቶች መሀበር ያዘጋጀው ነበር፡፡ ዮሐ.19÷23 ለዚህ ተግባራችው በምሳሌ 6÷31 ያለውን ሀሳብ እንደ መነሻ ይጠቀሙበት እንደነበር የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊዎች የስረዳሉ ፡፡
7.   በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት የተፈረደበት ሰው ደሙ ስለማይፈስ ባብዛኛው ከሁለት እስከ ሦስት ቀን ሳይሞት ሊቆይ ይችላል የሚሞተውም  በልብ ድካም ተሰቃቶ ነበር ፡፡ ሰዎች ስቃዩን አይተው እንዳያወርዱት በወታደሮች መስቀሉን ያስጠብቁ ነበር ፡፡ አልሞት ብሎ ብዙ ከቆየ ግን የቋንጃ አጥንቶቹን ሰብረው ይገላሉ፡፡ በክርስቶስ ግን ይህንን አላደረጉም በጦር ወጉት እንጂ፡፡ በነቢዩ ከአጥንቱ አንዲት አልተሰበረም ተብሎተ ነግሮዋልና፡፡ ዮሐ.19÷31-34   ማር. 15÷44
8.   በሰንበት ሰው አይሰቀልም ነበር ከሰንበት በፊትም የተሰቀለ ካለ ሰንበታቸውን እንዳያረክስባቸው ሰንበት ከመግባቱ በፊት በተለያየ መንገድ ቶሎ እንዲሞት ያደርጉና ይቀብሩታል፡፡ ዮሐ.19÷31-37
9.   የተሰቀለውን ሰው ልብስ ወታደሮች ይካፈሉት ነበር ፡፡ ዮሐ.19÷23
        ታሪካዊ ዳራውና በጊዜው በተለይም ጉታ ኢየሱስ በተሰቀለበት ወቅት የነበረው ሁኔታ ከላይ በዝርዝር ያየነውን ይመስላል ፡፡ በክርስትና የእምነት ጉዞ መስቀል ዋና ውና ማዕከላዊው ስፍራ ነው ፡፡
     በጽንስ ሀሳብ ደረጃ መስቀልን በሦስት ከፍለን ልናየው እንችላለን ፡፡
1.   እፀ መስቀል ( የእንጨት መስቀል)-ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ከእርጥብ እንጨት የተሰራ መስቀል ነው፡፡
                ይህ መስቀል ክርስቶስ ከተሰቀለበት ብኋላ ቅዱስ መስቀል ተብሎ ተጠርተዋል ፡፡ በክርስቶስ በግራና በቀኝ የተሰቀሉት ወንበዴዎችም እንዲሁ በእንጨት መስቀል ተሰቅለዋል ፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን የተሰቀሉበት የቁሳቁስ አይነት እንጨት ወይም ብረት መሆኑ ሳይሆን የተሰቀለበት ማን ነው የሚለው ነው ፡፡ የሽፍቶችን መስቀል የሽፍታ ካልን የክርስቶስን ደግሞ የመድሃኒታችን ነው እንላለን፡፡ከክርስቶስም የተነሳ የተሰቀለበት መስቀል የተቀደሰ መስቀል እንለዋለን ፡፡በክርስቶስ የሚያምን እያንዳንዱ አማኝና የእምነት ህብረት እንደ ነፃነት ምልክት ይቆጥረዋል ፡፡ ከጌጥነትም ባለፈ የእምነት ምስክርነት ነው ፡፡ መስቀልን ስንይዘው ስንነቀሰው ወይም ስንስመው በዚህ መስቀል ተሰቅሎ ባዳነኝ አምናለሁ ብሎ የልብን እምነት በአፍ እንደ መመስከር ነው ፡፡ ይህ ተውፊት በተለይ በምስራቃዊያን አቢያተ-ክርስቲያናት የተለመደ መንፈሳዊ ውርስ  ሲሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ለየት ያለ ስፍራ አለው ፡፡ የሰላም የእርቅ የፍቅር የነፃነት ፣የበረከት፤የጸሎት መጀመርያ፤ የድል ምልክት(ትዕምርት) ነው  አአትብ ገጽየ ወኩለንተየ በትዕምርተ መስቀል እንዲልየዘወትር ጸሎት፡፡

2.  መከራ መስቀል ( የክርስቶስ) -     በኢሳ 53÷1-ፍም   ስለ መተላለፋችን ቆስለ ስለ በደላችን ወደቀ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን ተብሎ አስቀድሞ በነቢይ እንደተነገረ የባሪያ መልክ ወስዶ፤ ከመላዕክት እንኳን አንሶ የሁላችንን ተግሳፅ ተቀብሎ ክርስቶስ አድኖናል ገላ 61 ብርቱ ዋጋም ተከፍሏል፡፡ ይኸ የዲያብሎስ አሰራር የፈረሰበት ጥል ከመንገድ የተወገደበት የክርስቶስ መከራውና ስቃዩ መስቀል ይባላል ፡፡ የተሰቀለበት መስቀል ለመዳናችን ማስታወሻ ምልክት ሲሆን መከራው፣ስቃዩና የደሙ መፍሰስ ግን ሕይወት ያገኘንበት፤ ጌታ ኢየሱስ  ስለ ኀጢያታችን ማስተስረያና ቤዛ ሆኖ የተሰጠበት ፤ታሪካችን የተቀየረበትና የእግዚአብሔር መለኮታዊ ዓላማ የተፈጸመበት የጽድቅ መንገድ ነው፡፡ ፡፡ በእርግጥም ኃጢያታችንን ለዘላለም ያስወገደበት በስቃይ እያማጠ ለክብር እኛን የወለደበትና ያዳነበት መስቀል መከራው ነው ፡፡ በመስቀሉ ጥልን ከመንገድ ጠርቆ አስወገደው እንደተባለ ይኸ ጥል የተወገደው በደሙ ፈሳሽነት በሞቱ፤ በመቃብሩና በትንሳኤው ነው፡፡ ስለሆነም የተሰቀለውን ደግሞም የተነሳውን ክርስቶስን እንሰብካለን፡፡ 1ኛቆሮ. 1÷17-25 ይህንን ጽሑፍ የምታነቡ ሁሉ የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በትኩረት እንድታነቧቸው አሳስባለሁ ፡፡ 1ኛቆሮ. 1÷17-25 ፊሊ.2÷5-ፍም ቆላ. 1÷19-20 ኤፌ.2÷14-16 ሮሜ 3÷25 ገላ.3÷13 ሮሜ 6÷1-11 ገላ.2÷15-20 ገላ.2÷24  ገላ.6÷14
·         ትኩረት፤- ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ የተናገራቸው ሰባቱ የመስቀል ቃላት በሀዲስ ኪዳን የመዳን ትምህርት ውስጥ ከፍተኛ ትርጉም የሚሰጣቸውና ከክርስቶስ የቤዛነትና የአርአያነት ስራ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ናቸው ፡፡ ሰፊ ዝርዝር ስለሚያስፈላጋቸው ዛሬ መነካካት ባያስፈልግም የሚገኙበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ልጠቁማችሁና በየግላችሁ እንድታጠኗቸው ደግሜ አሳስባለሁ ፡፡ በሌላ ጊዜ እግዚአብሔር ቢፈቅድ ምንአልባትም በሰሞነ ህማማት አካባቢ በዝርዝር የምንመለስባቸው ይመስለኛል ፡፡ 1. ሉቃ 23÷34 2. ዮሐ.19÷25 3. ሉቃ. 23÷43 4. ዮሐ.19÷28 5. ዮሐ.19÷30 6. ሉቃ. 23÷46 7. ማቴ. 27÷46

3. የክርስቲያን መስቀል
           ጌታ በወንጌል እያንዳንዱ መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ ነፍሱን ያተርፋል ማቴ.10÷24-25   በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማረበት በመዋዕለ ሥጋዌው በአንዱ ቀን ሁሉ ሊሸከመው የሚገባ የራሱ መስቀል እንዳለው አስገንዝቧል ፡፡ መስቀሌን ተሸክሙ ብሎ ቀንበር አልጫነብንም የእርሱን መስቀል ልንሸከም አንችልምና፡፡አቅም የለንም፡፡ ደግሞም እርሱ የመጨረሻውን የመስቀል አገልግሎት አንዴ ለዘለዓለም ፈፅሞታልና የክረስቶስን መስቀል ዳግም መሸከም አይቻልም አያስፈልግምም ፡፡የሚያፈልገው አንድ ነገር ቢኖር በተሰቀለው ማመን ነው፡፡ የሚያምኑት ግን የሆሳዕና ለመዘመር ብቻ ሳይሆን በሞቱም ለመተባበር ስለተጠሩ ሮሜ 61 በህይወት ውጣ ውረድ በአንድም በሌላም መንገድ የየራሳቸውን መስቀል  ይሸከማሉ፤ ፊሊ.1÷29 የተጠራነው አመኖ ለመኖር ብቻ ሳይሆን አመኖ ለመሞትም ነው፡፡ከባዱ ነገር አመኖ መኖር አይደለም፡፡ዕብ 1113
አማኞች ወደዚህ ህይወት የገባነው አስቀድሞ ተነግሮን ነው፡፤እኔን የተከተለ መከራ አለበት ተብሎ ልዩነቱ የአማኞች ፈተና የሚመጣው መውጫውን ይዞ ነው ፡፡በመጀመሪያ በማንም ላይ ሆኖ የማያውቅ ፈተና በእኛ ላይ አይሆንም ደግሞም ከምንችለው በላይ የሆነ መከራ እንድንሸከም ተላልፈን አንሰጥም ይመጣ ዘንድ ያለው ቢመጣ እንኳን ፈተናው ከመውጫው ጋር ተዘጋጅቶዋል፡፡ከሁሉም በላይ ግን በእግዚአብሔር ለሚያምኑ እንደ ሳቡ ለተጠሩ ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን፡፡፡1ኛቆሮ.10÷10  ሮሜ 828 የትም ቦታ መስቀል  ( መከራ፣ ፈተና ) አለ ፡፡ መከራው ላይቀር ዋጋ የሚያስጥ መከራ መቀበል ብልህነት ነው ፡፡ የእግዚአብሔር በረከት ያለው በመከራ ወረቀት ተጠቅሎ ነው ፡፡ የኤርትራን ባህር ሳይሻገሩ፤ በሲና በርሃ ሳያልፍ፣ በቃዴስ በርኔ ረሃብና ጥም ሳይፈራረቁብን ከንዓን አንገባም ፡፡ ወርቅ ወርቅ የሚሆነው በእሳት ተጠብሶ ነው ፡፡ እሳት አልፈልግ ካለ ግን ጭቃ ሆኖ መኖር ይችላል የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ በአማኞች ህይወት ፈተና በተለያየ ምክንያት ከተለያየ ቦታለመጣ ይችላል ፡፡
1.   ከሰይጣን የሚመጣ ፈተና - ይህ ዓይነቱ ፈተና እግዚአብሔርን አስከብረን መንፈሳዊ ተጋድሎ በመፈፀም የተዘጋጀውንም የድል አክሊል ለመቀበል የሚያበቃ በእምነት የምናድግበትና የምንነጥርበት መንፈሳዊ ትግል ነው ፡፡ በነገራችን ላይ በሰይጣን የሚፈተን ሰው የመንፈሳዊነት ደረጃው ላቅ ያለ ራሱን በራሱ ከመፈተን ያለፈ የሰዎችን ፈተና ያሽነፈ በአብዛኛው ሶስተኛው የመንፈሳዊ እድገት ላይ ( ፍፁምነት ) የደረሰ አማኝ የሚገጥመው አይነት ውጊያ ነው ፡፡
                መቼም ሰይጣን ጡረታ የማይወጣ ጠላት ነው ፡፡ የዘላለም ሀሳቡ የሰውን ዘር ሁሉ ማጥፋት ነው ፡፡ እርሱ ከጥንት ዘመን ጀምሮ ነፍስ ገዳይ እንደሆነ ቅዱሳት መጽሐፍት ይመሰክራሉ ዮሐ 844 ዘፍ 31-8 ፡፡ በኢዮብ ህይወት እንዳየነው ልጆቹን ከገደለ ሀብትና ንብረቱን አጥፍቶ እንኳን ስላልበቃው ሰውነቱን በቁስል መትቶ ፤ጓደኞቹ እንዲተውትና ሚስቱ እንድትጠላው አድርጎ እጅግ ፈተነው፡፡ ሰውነቱን ቆራርጦ ምላሱን ብቻ ተወለት ምላሱን የተወለትም ለኢዮብ አዝኖ ሳይሆን ስቃዩ ሲበዛበት እግዚአብሔርን ይሰድብልኛል ብሎ ስላሰበ ነበር ፡፡ ኢዮብ በእምነት እንደበረታ፣ በፈተናም እንዳልዛለ ባወቀ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ልጆች ጉባኤ ሔዶ የኢዮብን ነፍስ ለመነ ፡፡ እግዚአብሔር ግን በልጆቹ ነፍስ ፈጽሞ አይደራደርምና የኢዮብን ነፍስ ከለከለው ፡፡ ሰይጣን የሚፈልገው ገንዘባችንን፣ልጆቻችንን ወይም ሌላ ሌላውን ነገራችንን ሳይሆን ህይወታችንን ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ሰው አብርሃምም በልጁ በይስሃቅ ህይወት ነበር የተፈነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ሰይጣን መወራረድ የፈለገው በቅዱሳኑ ነፍስ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን ከፃድቃኖቹ ጋር ስለ ነበር የእግዚአብሔር ቅዱሳን ሁሉ በፈተና ነጥረው ወጥተው አክሊላቸውን ተቀብለዋል ፡፡
           እንደሚታወቀው ሰይጣን 7500 ዓመት በላይ የመፈተን፣የመጣል፣የመግደል ልምድ ያለው ባላጋራ ነው፤ ፍላጎታችን ውስጥ መሽጎ ከህሊናችን አጣልቶ ሲያሰቃየን ይኖራል ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ጥላችን ከሥጋና ከደም ጋር አይደለም  ከርኩስ መንፈስ ከከክፋት ሁሉ ሰራዊት ጋር ነው በማለት  የጦርነቱ ሁኔታ መንፈሳዊ መሆኑን ያስገነዘባል ፡፡ በመንፈሳዊ ውጊያ ደግሞ እንደ አቶሚክ ወይም ኒውክለር መሳሪያ ከባድ የማሸነፊያ መንገዶች ፆምና ፀሎት ናቸው፡፡ ጌታም በወንጌል እንዲህ ያለው ጋኔን ከፆምና ከፀሎት በቀር አይወጣም እንዳለ ፡፡ ስለሆነም ይህንን የጥፋት ሁሉ አባት ፤የርኩሰት ሁሉ እናት ማሸነፍ የምንፈልግ ከሆነ ከልማድ ፆና ፀሎት በተለየ መልኩ በሱባኤና በጽሞና በእግዚአብሔር ፊት መውደቅ ያስፈልጋል ፡፡ ሰይጣን የማይሸነፍ ጠላት አይደለም ተቃወሙት እርሱም ከእናንተ ይሸሻል ተብሎ ነው የተፃፈው ፡፡ አንዴ ተጥሏል የተጣለውን በእምነት መርገጥ ለአማኞች የተሰጠ የልጅነት ስልጣን ነው ፡፡ ዮሐ.1÷12 እምነት ደግሞ ምልክቶች ይከተሉታል፤ አጋንንትንም ያሸንፋል፤ የማንችለውንም ያስችላል ፡፡ማር 1616
2.   ከሰው የሚመጣ ፈተና - ክፉ ሰዎች በሦስት ይከፈላሉ ይባላል፡፡ ሰይጣን ያደረባቸው፤ ሰይጣን የሚያማክራቸውና ፍፁም ሰይጣን የሚመስሉ፡፡ ትልቅ ፀሎት ማለት ከእነዚህ ይጠብቀን ማለት ነው ፡፡ በቀላል ምሳሌ ለመረዳት በነብየ እግዚአብሔር ንጉስ ዳዊት ህይወት ውስጥ ተከሰተው የነበሩ ሁለት ፈተናዎችን እናንሳ ሀሳቦች ለማግኘት እንሞክር
            የመጀመሪያው የዳዊት ፈተና ጎልያድ ነው ሁለተኛው ሳኦል ነው ፡፡ ሳኦል የሚሸሸው ፈተና ሲሆን ጎልያድን ግን የግድ መጋፈጥ አለበት ፡፡ ምክንያቱም በጎልያድና በዳዊት መካከል ያለው ጦርነት ስለ እግዚአብሔርና ስለ ህዝቡ የመጣ ፈተና ነው ፡፡ የእስራኤልን ቅዱስ እየተሳደበ የመጣውን እስራኤልን ሊያጠፋ የሚፈልገውን ጎልያድን ከመጋፈጥ ውጭ ለዳዊት ምንም ምርጫ የለውም ፡፡ በቃ መጋፈጥ ነው ተጋፈጠው፡፡ ሳኦልን ግን መሸሽ መንፈሳዊነት ነው ምክንያቱም የሳኦል ችግር የዝና፣የገንዘብ፣የስልጣን፣የዙፋን ነው ፡፡ ሳኦል እንዲሁ ይለፋል እንጂ ዳዊት መንገሱ አይቀርም ስለዚህም ዳዊት ዘወር አለ፡፡ ከመጋፈጥም የእግዚአብሔርን ጊዜ መጠበቅ እንደሚሻል አመነ ብቻውን ዋሻ ውስጥ በጨለማ ስፍራ አግኝቶት እንኳን ሊገድለው አልፈለገም ሌሎቹንም ከለከለ እንጂ፡፡
           ይሄኛው አይነት ፈተና በአብቻኛው ሁለተኛው ደረጃ ላይ የሚገኙት ( ማዕከላዊያን ) ምዕመናን ላይ ተደጋግሞ የሚታይ ነው ፡፡ በክርስትና እድገት አደገኛው ደረጃ ነው ፤ወይ ፍፁም ሆኖ አልጨረሰ ወይ ወጣኒ ሆኖ ድካሙን አልተረዳ ነገሩን ሁሉ የእምነት ጉዞውን ጨምሮ ከሰዎች እንቅስቃሴ ጋር እያስተያየ የሚተገብርበት ፤ሲወድቁ የሚወድቅ፤ ሲነሱ የሚነሳ ፤ከብዙ ሰዎች ጋር ግጭት ውስጥ የሚገባ በሰዎች አብዝቶ የሚፈተን አይነት ሰው የሚገኝበት ደረጃ ነው ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለ ሰው አርቆ ማየትና የት ጋር እንደቆመ ማሰብ ካልቻለ ከእግዚአብሔር ክብር እስከ መጥፋት ሊያደርስ የሚችል ውጊያ አለው ፡፡ ለዚያም ነው ጌታ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ ፣ወንድሙን ማንም አይሳደብ ፣አያሰናክል ፍርዱ ታላቅ ነው እያለ አጥብቆ ያስተማረው ፡፤እንዲያውም በእግዚአብሔር መንግስት የመጨረሻው ፍርድ የወንጀለኛ መቅጫ ያደረገው የፍርዱ ምስክርነት ቃል ይሄንኑ በሰወች መካከል የለ ግንኙነትን ነው፡፡ተርቤ ተጠምቼ በማለት በሰወች የሚሆነው ሁሉ በእርሱ እንደሆነ አድርጎ ይቀጣበታል ይባርከበታል ፡፡
            ከዳዊት ልንወስደው የሚያስፈልገው ቀጥተኛ ትምህርትና በዚህ አውድ ትኩረት የሚሰጠው ዋና ሀሳብ ስለ እግዚአብሔር ክብርና ለቅዱሳኑ አንድ ጊዜ ስለተሰጠው ሃይማኖት መንፈሳዊ ትግል እንድንታገል ሲያስገነዝብ ነገር ግን ስለ ምድራዊ ክብር የሆነውን ማንኛውም ነገር ንግስና ቢሆን እንኳን እንድንሸሸውና እንድንፀየፈው ያስገነዝበናል ፡፡
3.   ከራስ የሚነሳ ፈተና - የሰው ጠላቱ ራሱ ነው ይላል ያገራችን ሰው ፡፡ በመንፈሳዊ ህይወት በተለይ ጀማሪ ( ወጣኒ ) የመጀመሪያው ደረጃ ክርስቲያን እያለን እጅግ አስቸጋሪው ነገር ከፍላጎትና ከስሜት የሚነሳው በመመኘት ምክንያት ሞትን የሚወልደው ኃጢያት ነው ፡፡ ያዕ.1÷12-15 ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ጉዳይ ሲገልጥ ስጋ በስጋ ህግ ፤መንፈስ በመንፈስ ህግ ይስበኛል ፡፡ የማልወደውን አደርጋለሁ የምወደውን አላደርግም በማለት የስጋ ድካምና የኃጢያት ጉልበት በሰው የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ውስጥ ምን እንደሚመስሉና ለመቆጣጠር ምን ያህል አስቸጋሪም እንደሆነ አስረድቷል ፡፡በርግጥም የጳውሎስ ህይወት ይህንን  ያህል ከፈተነው ከብዙመቻችን አንጻር ሲተይ ቀላል አይሆንም፡፡ ብዙ ጀግኖች ፣የተወደዱና የተከበሩ ሰወች፤ አገር መሪወችና ዝነኞችና የእግዚአብሔር ሰዎች ሳይቀሩ ከውስጥ በሚነሳ ማእበል ተሰናክለው ወድቀዋል፡፡እሰክ አስቡት አንድ ሰው ሲፈቀር የሚንቀባረረውን ያህል ሲያፈቅር እንደዛ መሆን የሚችል ይመስላችኋል  አይችልም ፡፡ከራሱ የተነሳ ፈተና ነውና፡፡
         አንድ አይነተኛ ለአብነት የሚሆን ታሪክ ደግሞ ከቅዱስ ዳዊት ህይወት እሁንም እንምዘዝ፣ የእግዚአብሔር ልብ የተባለው ዳዊት ጎልያድን ገሎ ሳኦልን ታግሶ እግዚአብሔር ካነገሰው በኋላ ቤርሳቤህ የምትባል ፈተና ስሜቱን ቀስፋ ያዘችው ሁሉን የረታው ዳዊት ልቡን መርታት አልቻለም ፤ሁሉን ያሸነፈው ዳዊት ስሜቱን ማሸነፍ አልቻለም፡፡ ቤርሳቤህን ወሰደ ረከሰ ፤ኦሪወንን አስገደለ በዚህ ምክንያት 70ሺህ እስራኤላውያን አለቁ፡፡
ራስን መግዛት ከመንፈስ ስራዎች አንዱና መሰረታዊ ከሚባሉት የሚጠቀስ ነው ፡፡ በርግጥ ራስን መግዛት አገር የመግዛት ያህል ቀላል አይደለም ፍላጎት ንጉስ በመሆንና  በጦር ሰራዊት ብዛት አይቆምም፡፡ ኑሮ ሒደት ነው አሁን ያለውን ማንነታችንም የተቀረጸው በሂደት ነው እኛነታችን ውሎ፣ትምህርት፣ዕድሜ፣ውድቀት፣ጓደኛ፣ቤተሰብበ በየጊዜው ውስጣችን ካስቀመጡት መልካምም ይሁን መጥፎ ነገር በመነሳት የዳብረው ስብዕና ነው ፡፡ ሁለችንም በሰለን ከሆነ የበሰልነው እንጨት ጨርሰን ነው፡፡በሂደት በእግዚአብሔር ርዳታ እንድ  ቀን ወደሚፈለገው  መንፈሰዊነት መድረሳችን አይቀርም ፡፡ስለዘህ ሰይጣን ዕድል እንዳያገኝና ሕይወታችንን እንዳይቆጣጠር  መጀመሪያ ደከማ ጎናችንን ለይቶ ማወቅ ከዘያም ተረጋግቶ ከችግሩ መውጣት ደግሞም ወደዚያው ላላመመለስ  መትጋት ይገባል፡፡ ለመንፈሳዊ ሰው ግን ራስን ከማሸነፍ የሚበለጥ ድል የለም ፡፡ በመነኮሳት መጽሐፍ አንድ ታሪክ ተጽፎአል ሁለት መነኮሳት በመንገድ ሲያልፉ ጥቅል ወርቅ ወድቆ አገኙ ፡፡አንዱ ለመነኩሴ ገንዘብ ምኑ ነው ብሎ አልፎት ሔደ አንዱ ደግሞ መልካም ስራ ብሰራበት መልካም እንጂ ብሎ አንስቶ ብዙ ድሆችን እየመገበ፣ አረጋውያን እየጦረ፣እጓለማውታን እየተንከባከበ ኖረ፡፡ ከብዙ ዘመን በኋላ እግዚአብሔር ለሁለቱም እኩል ክብር ሰጣቸው ፡፡ ገንዘብ ወሰዶ መልካም ስራ የሰራበት መነኩሴ እግዚአብሔርን ጠየቀ ለእኔ ይኸ አይገባኝም ይኸንን ሁሉ ሰርቸ ጓደኛየ ምን ስላደረገ ነው ከእኔ እኩል አለ ፡፡ ጌታም ያኔ ገንዘቡን ንቆ ራሱን ተቆጥሮ ሲያልፈው አንተ አሁን የደረስክበት ክብር ደርሶ ነበር አለው ፡፡    ስሜታችን የሚገዛን ሳሆን ሥሜታችንን የምንገዛ ያድረገን፡፡አሜን፡፡፡፡፡፡
  
መልካም ምንባብ


እባክዎትን ለሌሎች ሸር ያድርጉ !!!!