Wednesday, July 31, 2013

የመጀመሪያይቱ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት በቆሮንቶስ ላለችው የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን


መቅድም
‘’የእግዚአብሔርን ኃይልና የቅዱሳት መጻሕፍትን እውነት አታውቁምና ትስታላችሁ’’ ማቴ 22፥29

                    ቅዱሳት መጻሕፍት በእግዚአብሔር ፈቃድ ለትምህርትና ለተግሳጽ ይሆኑ ዘንድ በተለያየ ጊዜ በመንፈስቅዱስ ምሪት በተለያዩ  የእግዚአብሔር ሰዎች ተጽፈዋል:: ዘመናትን የተሻገረና የሚሻገር የእግዚአብሔር ኃይልና እውነት በውስጣቸው ስላለ ሕያዋን ናቸው፡፡ አሁን ባለንበት ዘመንም ብዞዎችን ወደ ሕያው አምላክ እያደረሱ ይገኛሉ::
ሰው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረ ነው፡፡ እግዚአብሔር በባሕርዩ አዋቂ ነው፡፡ሰው ደግሞ  ለማወቅ ፣ ለመረዳት ዝግጁ የሆነ አእምሮ ተሰጥቶታል፡፡ ስለዚህ መማር፣መመርመርና ማገናዘብ ተፈጥሮአዊ ግዴታው ነው፡፡ ሆድ ምግብ እንደሚፈልግ አእምሮም ለእውቀት የሚሆነውን እውነተኛ መረጃ ይፈልጋል፡፡ስለዚህም ነው እግዚአብሄር በገነት ውስጥ ለአዳም ያስተማረውን የቃል ትምህርት ትውልድ በምድር ላይ እየበዛ ሲመጣ በመጽሐፍ እንዲሆን ያደረገው፡፡ ዘፍ 2፥1-ፍጻሜ

        ሰው ቅዱሳት መጻሕፍትን ማጥናትና መመርመር ካልቻለ እውነቱን ከሐሰት፣ቅድስናን ከርኩሰት፣ ዘላለማዊውን ከጊዜያዊ፣ ሰማያዊውን አስተሳሰብ ከምድራዊ እንዲሁም መንፈሳዊውን አኗኗር ከሥጋዊ መለየት አይችልም፡፡ጌታችን ኢየሱስ አይሁድን የነቀፋቸው የእግዚአብሔርን ኃይልና መጻሕፍት የያዙትን እውነት ባለማወቃቸው ነው፡፡  በተሰሎንቄ እና በቤርያ ከተማ በነበሩት ሰዎች መካከል ሰፊ ልዩነት የፈጠረው ማወቅ የሚፈልግ አእምሮአቸውን ተጠቅመው ቅዱሳት መጻሕፍትን የማጥናት/መመርመር/  እና ያለማጥናት ጉዳይ ነበር፡፡ ሐዋ 17፥1-13 ተክርስቲያን መንፈሳዊት ተቋም ናት፡፡ ስለዚህም በቅዱሳት መጻሕፍት  እውነት ላይ የተመሠረተ ጥልቅ መንፈሳዊነት ሊኖራት ይገባል:: መንፈሳዊነቷን ሊመጥን በሚችል መልኩም በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ መደበኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስተምህሮ መርሐ ግብር ሊኖራት ይገባል ፡፡እውነተኛው ሕግ፣ ታሪክ፣ ጥበብ የሚቀዳው ከዚሁ አስተምህሮ ነውና:: 

       የዱባይ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያንም በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተመሰረተውን የእግዚአብሔር ዕውቀት አማኞች ሁሉ እንዲያውቁና እግዚአብሔርን በማወቅ ወደሚገኝ እረፍት እንዲደርሱ ስትተጋ ሰንብታለች ትተጋለችም :: እስከ አሁን ድረስ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስተምህሮ መርሐ  ግብር ላይ እግዚአብሔር ጸጋውን ያበዛላቸው ብዙ መምህራን ተሳትፈዋል፡፡ ብዙውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም አስጠንተዋል፡፡እግዚአብሔር መሻትንም ማድረግንም ሰጥቶን  መጀመሪያይቱ የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች  መጽሐፍ ጥናት አሁን ባለንበት ወቅት በመምህር በሪሁን ወንድወሰን  ስናጠና ስንብተናል :: በነበሩን ጥናቶች ሁሉ ላይ ጸጋውን ያላጓደለ አገልግሎቱን በቅዱስ መንፈሱ ይመራና ይቆጣጠር የነበረ አምላክ ምስጋና ይድረሰው፡፡ለመምህራኑም  ጸጋውን ያብዛላቸው፡፡

      የቆሮንቶስ ምዕመናን ሕይወት አሁን እኛ ከምንኖርበት አኗኗር ጋር እጅግ የተነጻጸረ ከመሆኑም በላይ የዛሬዋ ዓለምና ርኩሰቶቿ በሚያስገርም ሁኔታ የዚያች ከተማ ግልባጭ እስኪመስሉ ድረስ አንድ ዓይነት ሆነዋል :: ቤተክርስቲያን ርኩሰት በበዛበት በዚህ ዓልም ውስጥ የምትገኝ መንፈሳዊ ተቋም እንደመሆኗ መጠን መንፈሳዊ ውበቷን ይዛ እንዴት መኖር እንዳለባት ስለመንፈሳዊና አስተዳደራዊ ውሳኔዎች፣ እንደ ሥጋ ወደሙና ትንሣኤ ሙታንን የመሰለ ጠንካራ መለኮታዊ ሀሳቦችን መንፈስ ቅዱስ አስተምሮናል::

    እያንዳንዱ ምዕራፍ በርዕስ ተከፋፍሎ ትምህርቱ መሰጠቱ አዲስ የአቀራረብ መንገድ የፈጠረ ሲሆን አጠቃላይ ጥናቱ በሚከተለው መንገድ ቀርቧል፡፡
  1. ሊቃውንት የዮሐንስ አፈወርቅ የአተረጓጎም ስልት የሚሉትን (መጽሐፍ ቅዱስን በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ሀሳብ መተርጎም) ተከትሏል፡፡
  2.  በሌሎች ክፍሎች ያሉ ተመሳሳይ ሀሳቦች እንዴት ሊገነዛዘቡና ሊጣመሩ እንደሚችሉ በምስጢራዊ ይዘትም ምን ያህል አንድነት እንዳላቸው ለማሳየት ተችሏል:: ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ  ሰዎች ቢጻፍምና በተለያየ ጊዜ ቢከተብም ሀሳቡ ግን የዘላለም እውነት እንደሆነ ለማስረዳት ተሞክሯል:: 
  3. በዚያውም  ምዕመናን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ለመዳሰስ እንዲሁም የማንበብ አድማስንና መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ልምድን እንዲያሳድጉ የተለየ መንገድን አሳይቷል፡:
       ይህንን ትምህርት ቤተክርስቲያናችን ለምዕመናኖቿ ካስተማረች በኋላ የተሻለ መንፈሳዊ ለውጥ ይኖራል ብዬ አምናለሁ:: መንፈስ ቅዱስ በብዙ ጸጋ ረድቶን ነበርና:: ይህ አገልግሎት በሚሰጥበት ጊዜ በልዩ ልዩ  መንገድ ያገለገላችሁትን ሁሉ የቤተክርስቲያን አምላክ በመንፈሳዊና በሥጋዊ በረከት መንፈሳዊና ሥጋዊ ኑሯችሁን ይሙላ::
እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅ አገልግሎቷን ያስፋ፡፡
ቀሲስ ተስፋ እንዳለ

የ ዱ/ቅ/ሚ/ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ አስተዳዳሪ

1 comment:

  1. emperor casino no deposit bonus 2021 - Shootercasino
    Emperor Casino has all the games you could want, including free spins, cashable deposit bonus and a lot of 제왕 카지노 가입 쿠폰 other bonus offers from the best online

    ReplyDelete