Thursday, October 30, 2014

ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ፀልዩ



              ፀልዩ
                             ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ፀልዩ    ማቴ.26÷41
      ራሱ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ በቀጥታ የተናገረው መለኮታዊ ትዕዛዝ ነው ፡፡በሀዲስ ኪዳን መፅሐፍት ውስጥ ከታወቁት ስድስቱ ቃላተ ወንጌል በተጨማሪ ከ600 በላይ ቀጥተኛ የቅድስና ትዕዛዛት አሉ ፡፡ ለምሳሌ፤- ሊደረግብህ የማትፈልገውን በሰው ላይ አታድርግ ፤ ፁሙ ፣ ፀልዩ ፣ ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ ፣ባላጋራህን እንደ ራስህ ውደድ ፣ ካባህን ከወሰደ መጎናፀፊያህን ጨምርለት ወዘ.ተ እነዚህ ቀጥተኛ ትዕዛዛት ህግ ባይሆኑም እንኳን ከህግ የተሻለ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር ሀሳብ የሚያቀርቡ የቅድስና መንገዶች ናቸው ፡፡ ሌሎቹን ለጊዜው ተወት እናድርጋቸውና ወደ ዋናው የዛሬው ትኩረታችን ወደ ፀሎት እንመለስና አንዳንድ ነገር እንገንዘብ ፡፡
      የዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በጥልቀት ስንመረምር የፀሎትን ኃይል፤ጉልበት፣ መፍትሄ ሰጭነትና ሁለንተናዊ መንፈሳዊ መሳሪያነት ፍንትው አድርጎ ያሳየናል ፡፡ ጊዜው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመስቀሉ 18 ስዓት ቀደም ብሎ ነው ሁሉም ነገር ተጠናቋል የቀረው አንድ ነገር ብቻ ነው የጌታ ተላልፎ መሰጠት ፡፡ በዚህ አስጨናቂ ጊዜ በሞትና በህይወት መካከል የሰከንድ ሽርፋፊ ብቻ ቀርቶ እንኳን ጌታ ይፀልይ ነበር ሐዋርያትንም በርትተው እንዲጸልዮ አበክሮ አሳስቧቻው ነበር ያውም በትጋትና ያለማቋረጥ ፡፡ ይህ ማለት ፀሎት በከፍኛ ትጋት የሚፈፀምና የማይቋረጥ ለነፍስ ከኦክስጂን በላይ አስፈላጊ ነገር ነው ማለት ነው ፡፡ የሚያምን ሰው ከአምላኩ የሚገናኘው በፀሎት ነው እግዚአብሔር በቃሉ በኩል ይናገራል አማኝ ደግሞ በጸሎት ይመልሳል ፡፡ፀሎት የለም ማለት ግንኙነት ተቋርጧል ማለት ነው ፡፡ህይወት ከሚሰጠው የተለየ ደግሞ ህያው መሆን አይችልም ፤ አሳ ከባህር ከወጣ ፤ ቅርንጫፍ ከዛፉ ከተለየ ፤ አምፖልስ ከጀነሬተሩ ጋር የሚያገናኘው ከሌለ ምን ህይወት አለው ምንም፡፡ ስለዚህ ፀሎት በስህተት እንኳን የምናቋርጠው ነገር አይደለም ፡፡ ስዓት ቆጥረን እንደ ስራ ወይም መከራ ሲበዛብን እንደማምለጫ የምንጠቀመው የእንቅስቃሴያችን አንድ ክፍል ሳይሆን በእያንዳንዱ የህይወት መንገድ እግዘአብሔርን እያከበርን የምንኖርበት የአምልኮ መገለጫ ነው የህይወት ዘመን ሙሉ መንፈሳዊ ለምምድ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በእያንዳንዱ የሰከንድ ሽርፍራፊ ማሰብ ፀሎት ነው ፡፡ ታላቅ ፀሎትም ነው ፡፡ የቀደሙት የእግዚአብሔር ሰዎችን ህይወት ስናጠናም በፀሎት እጅግ ድንቅ እንዳደረጉ እናውቃለን ፤ ጌታም በወንጌል በፆምና በፀሎት ምን ያህል ኃይል እንደሚደረግ አጋንንትንም ማሸነፍ እንደሚቻል አስተምሮናል ፡፡ ማቴ.17÷21
      በእግዚአብሔር ፊት ለጸሎት በምንቆምበት ጊዜ የግድ ሊጤኑ የሚገባቸው ነገሮች አሉ ፡-
1.   በመንፈስ ሆኖ መፀለይ ፡- ፀሎት ድጋም አይደለም ፡፡ ፀሎት የመንፈስ መነጠቅ ነው ፤ ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መገታኘት ብቻ አይደለም መነካካትም ጭምር እንጅ፡፡ ፀሎት ከነፍስ የሚከፈል ወደ ተለየ ዓለም የሚነጥቅ ልዩ ጣዕም ያለው በስጋ ሀሳብ ሊገለጥ የማይችል የተለየና ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ መለኮታዊ የግንኙነት መስመር ነው፡፡ አንድ መጽሐፍ ገልጦ ከመግቢያው እስከ ማሳሰቢያው ማንበብ ፀሎት አይባልም ፡፡ አበው የዘንድሮ ፀሎት አይን ፊደል ይነዳል ልቤ ቤት ያሰናዳ ነው  እንዲሉ፡፡በጸሎት ጊዜ ሀሳብን መሰብሰብ፤መመሰጥ፤በተቻለ መጠን ከጸሎት አስቀድሞ በጸሎት መሀል እየተመላለሱ ለሚረብሹ ሀሳቦች ለጊዜውም ቢሆን መፍትሄ መሰጠት ያስፈልጋል፡፡
2.         በእምነት ሆኖ መፀለይ ፡- አምናችሁ የምትፀልዩበትን ሁሉ ትቀበላላችሁ ፡፡ የምንፀልየው ተስፋችንን ሳይሆን እምነታችንን ነው ፡፡ ምንም ነገር ቢሆን ስለሰጠኸን፣ ስላደረክልን እንላለን እንጂ ስለምታደርግልን ብለን ቀጠሮ አንይዝም ፡፡ በቃ ስንፀልይ አባታችን  ሰምቶናል መልሱን ለልጆቹ መስጠት ደግሞ ያውቅበታል ማቴ 6፤8-9፡፡ በፀሎት የጠየቅነውን አምነን እርግጠኛ የሆንበትን ነገር ባንቀበልስ ከተባለ እርሱማ ስለማይጠቅመን እግዚአብሔር የከለከለን ነው ፡፡ ይኸ ደግሞ ከመቀበል እኩል ነው ፡፡ በነገራችን ላይ ልመና በፀሎት ክፍል ውስጥ በጣም ትንሹና የግድ አስፈላጊ ያልሆነው ክፍል ነው ፡፡ የለመነውን የግድ ማግኘት አለብን ብለን ከእግዚአብሔር ጋር ሙግት ከገጠምን ግን ብንቀበል እንኳን ፍቃዱ ሳይሆን የወሰድነው ነገር ያጠፋናል ፡፡ 1ኛ ሳሙ.8÷7 እንደፈቃድህ ይሁን ብሎ ምንፀለየውም ለዚህ ነው ፡፡ለሚያምን ሁሉ ይቻላል ለማያምን ደግሞ ምንም አይቻልም፡፡
3.          በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መፀለይ ፡- ጌታ በወንጌል በስሜ አልፀለያችሁምና አልተቀበላችሁም ብሏል ፡፡ ፀሎት ሁል ጊዜም ወደ ሥላሴ መንግስት ይቀርባል ፤ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስም በዙፋናቸው የእያንዳንዱን ልመናና ፀሎት ያደምጣሉ፣ ይፈርዳሉ፣ ይመግባሉ፣ ያስተዳድራሉ … አማኞችም የዳኑት በሥላሴ መንግስት ውሳኔ ስለሆነ ( በእርሱ ፈቃድ ፣ በአባቱ ፈቃድ ፣ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ) መጥቶ አዳነን እንዲል ፤ በዚህ ድህነት የእግዚአብሔር ልጆች ሆነዋልና በዳኑበት ስም ፣ በዳኑበት ደም ፣ በዳኑበት አምላክ ይፀልያሉ ፡፡በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መፀለይ ማለት  ክርስቶስ የከፈለው የማዳን ዋጋ ዛሬም ህያው ነው ብሎ ማመን ፣ ወደ ቆምንበት ወደዚህ ፀጋ እንዴት እንደባን ማስታወስ ወይም አሁን እንኳን ወደ እግዚአብሔር ለመፀለይና በፊቱ ለመቆም  የቻልነው ጥል ስለተወገደ  ነውና ይህንን ጥል ያስወገደልንን ጌታ እያሰብን ባገኘነው የልጅነት ክብር አባ አባት እያልን እንፀልያለን ዮሐ 16፤26-27 ፡፡ ጌታ ራሱ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል እንዳለ ዮሐ 15፤16 ፡፡ በእለተ አርብ መስዋዕት በሆነ ጊዜ፣ ራሱም መስዋዕት አቅራቢ ብቻ ሳይሆን ተቀባይም እንደነበር ከእግዚአብሔር ጋር በታረቅንበት በክርስቶስ ስንፀልይም በስሙ የተፀለየውን ፀሎት በሥላሴ መንግስት አንዱ ወልድ ከመንፈስ ቅዱስና ከአብ ጋር ጸሎታችንን ይቀበላል ፡፡ ወደ ሥላሴ የደረስነው በክርስቶስ  ነው እለት እለትም የምንደርሰው ከክርስቶስ የተነሳ ነው፡፡                                                                                                                             

ፀሎት አራት መሠረታዊ ክፍሎችን ያጠቃልላል
      ሊቃውንት እንደሚሉት ብዙ ጊዜ ከመለመን አንድ ጊዜ ማመስገን ይሻላል ፡፡ በመሆኑም የመጀመሪያው የፀሎት ክፍል ምስጋና ነው ፡፡ የምስጋና ኃይል የትኛውንም የተዘጋና የተቆለፈ ነገር መክፈት ይችላል ፡፡ እግዚአብሔር ከሁሉም በላይ በአመስጋኞች እጅግ ደስ ይለዋል ፡፡ በሁሉ ስለ ሁሉ አመስግኑ ተብሎ እንደተፃፈ ፡፡ አማኞች በፀሎታቸው ጊዜ ሊዘነጉት የማይገባውና ዋነኛው ክፍል የምስጋና ክፍል ነው ፡፡ ምስጋና አራት የተለያዩ ክፍሎች ይኖሩታል ፡-
1. እግዚአብሔርን ማመስገን ፤-ስለ ፍጹም አንድነቱ፤ስለመለኮታዊነቱ ፣ ስለ ሀልወቱ ፣ ስለ ታላቅ ችሎታው ፣ ስለ ማይወሰን ኃይሉ ፣ እጅግ ግሩም ስለሆነው ባህሪው ማመስገን ፣ ለምሳሌ፡- የዘላለም አባት  ጌታ እግዚአብሔር አምልካችን ሁሉን ስለያዝክ ፣ ሁሉን ስለምታኖር ፣ የሚታየውንና የማይታየውን ስለፈጠርክ ፣ ከሀረፃንነታችን ጀምሮ ስለጠበቀን ፣ በብዙ በረከት ስላሳደከን ፣ እጅግ ሩህሩህና ይቅር ባይ ፣ አፍቃሪና የዋህ ስለሆንክ ፣ ስለማይነገረው ስጦታህ ሁሉ እናመሰግንሀለን ፡፡ደገሞም አባትነትህን እንድንረዳ አምላክነትህን እነድናውቅ ስለረዳህን አንተን በማመን ወደመገኝ ህይወት ስለደረስከን አንተን በመስማት ወደሚገኝ ረፍት ስለመራሀን እናመሰግነሀለን ፡፡ልንል እንችላለን ፡፡
        2.የሥላሴን መንግስት ማመስገን ፡- መንግስትህ ትምጣ ብለን መጸለይ እንዳለብን ክርስቶስ አስተመሮናል፤፤ የእግዚአብሔር መንግስት ማለት ሁለንተናዊ የእግዚአብሔር አስተዳደር ማለት ነው ይህ መለኮታዊ መንግስት በሶስት አካላት በአንድ ዘላለማዊ ስልጣን የሚመራ ነው፡፡ስለሆነም ይህንን ተወዳጅ አምላክ ታለቅ ጌታ ዘላለማዊ ንጉስ ከላይ በጥቅል እግዚአብሔር ያልነውን አምላክ በተለየ አካሉና ባህሪው ማመስገን አስፈላጊ ነው፡፡
 ለምሳሌ ፡-    .  የጌታችንና የመድሃኒታችን አባት እግዚአብሔር አብ አምላካችን እናመሰግንሀለን፤- ከስጦታ በላይ የሆነ ስጦታ የተወደደ ልጅህን ስለ ኃጢያታችን ይቅርታ ይሞትልን ዘንድ ስለሰጠኸን ፣ በአንድ ልጅህ ጨክነህ እኛን ሞት የሚገባንን ስላዳንከን፤ መንግስትህ ለዘላለም ስለሆነች፤ ለግዛትህም ልክና ወሰን ስለሌለው ፡ የማትተረጎም፡ የማትተረክ፣ የምትደነቅና የምታስገርም፤ የምትወደድና የምትፈቀር ስለሆንክ ከእኛ በላይ ለእኛ ስለምታስብ እንደ አይን ብሌን ስለምትጠነቀቅልን እናመሰግንሀለን፡፡ልንል እንችላለን፡፡
·         ጌታችን መድሀኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናመሰግንሃለን፣ ስለነዚያ ችንካሮች ፣ እየተራብክ ስላጠገብከን ፣ እየተጠማህ ስላጠጣኸን ፣ ራቁትህን ሆነህ በፀጋ ስላለበስከን ፣ ወደ መንግስትህ ስላፈለስከን ፣ በተሰበረው በኩል ሁል ጊዜ ስለምትቆምልን ፣ እናትም አባትም እህትም ወንድምም ሆነህ ስለደገፍከን ፣ በደምህ እየጋረድህ የሰይጣን ምክሩን እያጠፋህ በህይወት እንድቆም ዛሬን እንዳየው ስለረዳህን እናመሰግንሃለን፡፡ ልንል እንችላለን ፡፡
·         ጌታ መንፈስ ቅዱስ ሆይ ስለ አምላክነትህ ፣ ስለ አጽናኝነትህ ፣ ስለ ምህረትህ ፣ እናመሰግንሃለን ፤ የኃይል መንፈስ፤የእውቀት መንፈስ፤የእውነት መንፈስ ፣ የጽድቅ መንፈስ ፣ የይቅርታ መንፈስ ፣ የፍቅር መንፈስ ፣የህይወት መንፈስ፤የእግዚአብሔር መንፈስ፡፡ ቤተክርስቲያንን ለሙሽራው ኢየሱስ ሰርግ የምታዘጋጅ፣ የምታስውባት ፣ የምታነፃት አንተነህና ክብር ይገባሀል ፡፡ በእውነት የቀደሙትን አባቶች ስላገዝክ ፣ አለማትን በወንጌል እንዲከድኑ ፣ የአላውያንን መከራ እንዲታገሱ እውቀትና ጥበብ ፣ ጽናትና ድፍረት ፣ ጥበብና ትምክህት ስለሆንካቸው እኛንም በነገር ሁሉ እንዲከናወንልን ስለረዳኸኝ አመሰግንሀለሁ፡፡ ልንል እንችላለን ፡፡
                  3.እግዚአብሔርን ስለ ትድግናው  ( ስለ ጥበቃው ) ማመስገን ፡- ለምሳሌ ፡- ጌታ ሆይ ዛሬ በህይወት መኖሬ ይገርማል ፡፡ ስታመም አልጋየን አንጥፈህ ፣ ስወድቅ ቀድመኸኝ ወድቀህ ፤ የማይወጣውን እንድወጣ ጉልበት ሆነህ አኖርከኝ ፣ ከንፈሬን በእልልታ ፤ አፊን በምስጋና ሞላህ ፣በአውሎና በወጀብ አሳለፍከኝ ፣ የተቆረጠውን ሁሉ ቀጥለህ ፀሐይ አወጣህልኝ ፡፡ መከራየን ሁሉ እንዳለፈው ክረምት አሳለፍከው ተመስገን ፡፡ ባእድን ዘመድ ፣ ክፉውን መልካም፣ እያደረግህ ስንት ጊዜ ረዳኸኝ ስንት ጊዜ አስመለጥከኝ፣ ስንት ጊዜ አሻገርከኝ ፣ስንት ጊዜ ተከራከርክልኝ፣ ስንት ጊዜ አሸነፍክልኝ፣ ስንት ጊዜ ተመካሁብህ የኔ ጌታ ሲያልፍ ቀለቀል ይመስላል እንጅ አንተ ከእኔ ጋር ባትሆንማ ያ ሌሊት አይነጋም ነበር ፤ አባቴ፣ መድሀኒቴ ፣ ወዳጅ ፣ ከፍ በልልኝ፡፡ ልንል እንችላለን ፡፡
                    4.እግዜአብሔርን ስለ ስጦታው ሁሉ ማመስገን ፡- ለምሳሌ ፡- ሁሉ ካንተ ፣ሁሉ ባንተ፤ ሁሉ ለአንተ ነው ፡፡ ከእኔ የሆነ ምንም ነገር የለም ሥራየን የሰራኸው ፣ ብርሃኔን ያበራኸው አንተነህ ፣ የሚበላና የሚጠጣውን ፣ ትዳርና ልጆችን ያገኝሁት ካንተ ነው ፣ እንዲህ የተትረፈረፈልኝ ቤቴ ስለገባህልኝ ነው ፣ ቆጥሬ የማልጨርሰውን የተቀበልኩት ካንተ ነው ፣ ተመስገንልኝ ፡፡ ካንተ ያልሆነ ምን አለ፣ በህይወቴስ ካንተ ሌላ እንዲህ አረገልኝ የምለው ማን አለ ? ክብሩን ሁሉ ጠቅልለህ ውሰድ ፣ የሰጠኸኝ ሁሉ ለአንተ ክብር ይሁንልኝ ፡፡ ባበዛህልኝ ነገር እንዳልፈተን ጠብቀኝ፤ ምስጋና ይብዛልህ፣ አምልኮ ይብዛልህ፤ ሁሉ ከእግርህ በታች ይንበርከክ  ምስጋና ላንተ ብቻ ይሁን ፡፡ልንል እንችላለን ፡፡
ሁለተኛው የፀሎት ክፍል ኑዛዜ ነው ፡፡ ኃጢያቱን የሚናዘዝ ይለማል የሚሸሽጋት ግን ይጠፋል  እንደተባለ ኃጢያትን መናዘዝ፤ ላጠፉት ጥፋት ኃላፊነትን መውሰድ፣ ኃጢያትን መተውና ደግሞ ላለማድረግ መወሰን የእዉነተኛ መጸጸት ወሳኝ  ክፍሎች ናቸው ፡፡ በፀሎትም ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት መናዘዝና የኃጢያት ይቅርታ መጠየቅ የክርስስቲያንዊ ኑሮ የእለት ተእለት ክንውን ነው፡፡
 ሦስተኛው የፀሎት ክፍል ልመና ነው ፡፡ ልመና በሁለት ይከፈላል ፡፡ የመጀመሪያው ከላይ ለተናዘዝነው ኃጢያት ይቅርታ መለመን ነው፡፡ለምሳሌ ፡- አባት ሆይ ኃጢያቴና በደሌ እጅግ ብዙ ነው አሁን በዚህ ሰዓት እንኳን በፊትህ ቆሜ ብዙ በድያለሁ ፡፡ የማልወደውን ነገር እያደረግሁ የምወደውን ነገር ለማድረግ አቅቶኛል እባክህ አለማመኔን እርዳው ምህረትህን ተስፋ አደርጋለሁ፣ ይቅርታህን ፣ አባትነትህን ፣ ፍቅርህን ፣ አይተህ ይቅር በለኝ ፡፡  ማንም በፊትህ ንጹህ አይደለም ፤ ከሁሉ ደካማ ነኝ አንተ ይቅር ካላልከኝ ምንም አይወደኝም ወደየትስ እሄዳለሁ ፡፡ የላየን ሳይሆን የውስጤን ፣ የአፊን ሳይሆን የልቤን የምታውቅ በፊትህ ራቁቴን ሆኛለሁና ፈራሁ እባክህን ይቅርታህን ስጠኝ ፡፡ ስለ ስህተቴ ሰበብ የለኝም ሁሉን ወድጄና ፈቅጀ አድርጌያለሁ ኃጢያቴን አምናለሁ ጌታ ሆይ ይቅር በለኝ፡፡ልንል እንችላለን፡፡                                                                                                                                    .            ሁለተኛው ደግሞ በእለቱ በእግዚአብሔር ፊት ይዘነው ለቀረብነው ርዕሰ ጉዳይ ላይ በአምላካችን ፊት ልመና የምናቀርብበት ክፍል ነው፡፡ጸሎት በርዕስ ነው ሚጸለየው፡፡አንዳንድ ጊዜ በአንድ ሰዓት ስለ ብዙ ነገር ስለምንለምን ለጸሎታችን መልስ ተሰጥቶን እንኳን ያገኘነው መልስ በህይወት አጋጣሚ የመጣ እንጅ የጸሎታችን መልስ ላይመስለን ይችላል ፡፡ስለዚህ ወደፊት እግዚአብሔርን ለማመሰገኛም ተጨማሪ ምክንያት ይሆን ዘንድ ልመናችንን በርዕስ በርዕስ መለየት ያስፈልጋል ፡፡የፀሎታችንም አይነት እንደያዝነው ርዕስ የተለያየ የሆናል፡፡ለምሳሌ፡- የእለቱ የጸሎት ርእሳችን ፈውስ ስለማገኘት ቢሆን እንዲህ ልንል እንችላላን፤- አምላኬና አባቴ እግዚአብሔር ሆይ የመኖሪያ መንገዶች ሁሉ አዳሽ የተሰበሩ አጥንቶቸን ሁሉ የምትጠግን ስምህ መድሀኒት፣ ቃልህ መድሀኒት፣ መጎናፀፊያህ መድሀኒት የሆነ ዛሬ ወደ ህይወቴ ወደ ድካሜ ወደ ህመሜ እንድትመጣ እለምንሃለሁ፡፡ መጻጉን የፈወሰን፤አልአዛርን ከመቃብር የቀሰቀሰውን፤12  ዓመት ሙሉ ደም የፈሰሳትን ሴት ደም ቀጥ አድርጎ ታሪኳን የለወጠውም ድምጽህን አሰማኝ፡፡
አራተኛውና የመጨረሻው የፀሎት ክፍል ዲያብሎስን መቃወምና መገሰጽ ነው ፡፡ ዲያብሎስን ተቃወሙት እርሱም ከእናንተ ይሸሻል ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ያከብራችኋል እንደተባለ፤ በስሙ መቃወምና መገሰጽ ያስፈልጋል ፡፡ ለምሳሌ፡-በፊታችን ያለ የክፉ ሰወች ሃሳብና የሰይጣን አሰራር ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከመንገዳችን ይወገድ፤የጠላት ምክሩ ይፍረስ፤ሙዋረተኛ አስማተኛ ጠንቋይ ሴራው ሁሉ የአኬጦፌ መክር ይሁን፤እግዚአብሔርን የሚቃወሙ ሁሉ  ይበተኑ ሰማጠራራቸው ይጥፋ፡፡እግዚአብሔርም ለጆቹን ከአጋንንት አስራር ሁሉ ለዘለአለም ይታደጋል አሜን፡፡በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፡፡ልንል እንችላላን፡፡፡
በመጨረሻም አባት ሆይ ጸሎታችንን ስለሰማከን እናመሰግንለን፤፤ምስጋና ይሁን አንድ አምላክ ለሚሆን ለአብ ለወልድ  ለመንፈስ ቅዱስ ዛሬም ዘወትርም ለዘለአለም፡፡አሜን!!!በማለት ጸሎታችንን ልናጠናቅቅ እንችላላን፡፡                                                                   ማሳሰቢያ፤-ለምሳሌ ተብለው የቀረቡት ጸሎቶች ለምሳሌየቀረቡናቸው፡፡                                                                                                                                       
እባክዎ ሌሎችም ሸር በማድረግ አገልግሎቱን በማዳረስ የበኩልወን ይወጡ፡፡