Friday, August 23, 2013

የመጀመሪያይቱ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት በቆሮንቶስ ላለችው የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን መግቢያ



የመጀመሪያይቱ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት
በቆሮንቶስ ላለችው የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን
መግቢያ
v  የቆሮንቶስ ከተማ
መልክዓ ምድር:
·         ከግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ 75 ኪ.ሜ ትርቃለች
·         በሁለቱ የግሪክ ጠቅላይ ግዛቶች /አኪያና መቅዶኒያ/ መካከል ባለው ልሳነ ምድር ላይ የተገነባች ከተማ ነበረች
·         የአካያ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማም ነበረች
·         የሮማው ምክትል ቆንሲል መቀመጫም ስለነበረች ብዙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ነበሩባት
1.   ንግድ
·         በብዙ የባሕር ወደቦች የተከበበች ከተማ በመሆኗ ከልዩ ልዩ  የዓለም ክፍል የተሰበሰቡ ነጋዴዎች በከተማዋ ይኖሩ ነበር። በዚህም ታላቅ የንግድ ማዕከል ሆነች
·         ከሮም ወደ ምስራቅ ለሚደረገው ታላቅ የንግድ ጉዞ ሁነኛ የባሕርይ መሸጋገሪያ ነበረች
·         ከብልጥግናዋ እና ከስልጣኔዋ የተነሣ እጅግ የከፋ ኃጢአት የሚደረግባት ከተማ ሆነች። ከዚህ የተነሣ ቆሮንቶሳዊ መሆን የእፍረት ምክንያት እስከመሆን ደርሶ ነበር።
·         ቆሮንቶስ በራዕይ ዮሐንስ ላይ የተጠቀሰችውን ባቢሎን እስክመምስል ደርሳ ነበር  ራዕ 18፥2፤ ራዕ 17፥5
2.   ሃይማኖት
·         የተለያዩ  ሃይማኖቶች የአይሁድ እምነትን ጨምሮ  በከተማዋ ነበሩ
·         ከ20 በላይ የጣዖት መቅደሶችም ነበሩባት
·         የአይሁድ ምኩራብም እንዲሁ በዚያው ነበር   ሐዋ 18፥1
·         አፍሮዲቴና leእርሷ የተቀደሱ 1000 ሴተኛ አዳሪዎች ነበሩ   ሮሜ 1፥26
3.   ማኅበራዊ እንቅስቃሴ
·         ከንግድ ከተማነቷ ጋር ተያይዞ ስፖርት፣ ቲያትር  እና ሥነጥበብ በቆሮንቶስ ይዘወተሩ ነበር
·         ሮማውያን፣ አይሁዶችና ግሪኮች የሚኖሩባት ከተማ በመሆኗ ማኅበራዊ እንቅስቃሴውና ባሕሉ ቅይጥ ነበር
·         አብዛኛዎቹ ነዋሪዎችና ነጋዴዎች ግሪኮች ስለነበሩ የከተማዋ የሥራ ቋንቋ ግሪክኛ ነበር
·         ሐዲስ ኪዳን ወደ አሕዛብ ምድር ከገባበት ዘመን 600 ሺህ ሕዝብ የሚኖርባት ታላቅ ከተማ ነበረች።
v  የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን
·         በሐዋርያው ጳውሎስ ሁለተኛ የወንጌል ጉዞ  ተመሰረተች።  ሐዋ 15፥36፤ 16፥6
·         ጊዜው ከ50-52 ዓ.ም ሲሆን በዚህ ወቅት ጳውሎስ በቆሮንቶስ ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በላይ ተቀምጧል። 
·         በምኩራብም ተሳዳቢዎች ስለበዙ ያመኑትን ነፍሳት ለይቶ በአንድ ግለሰብ ቤት በማስተማር አገልግሎቱን ጀምሯል   ሐዋ 18፥6
v  የቆሮንቶስ ክርስትና
·         ለፍጹማን እንኳን ፈታኝ የሆነ ትግል ውስጥ ነበረች
·         የቆሮንቶስ ከተማ ቤተክርስቲያን ውስጥ ገብታ ነበር
·         አብዛኞቹ ድሆችና ጥቂት ባለጠጎች የነበሯት ቤተክርስቲያን በመሆኗ ቆሮንቶሳዊneት /መለያየት/   ገላ 5፥21 ለተባለው ኃጢአት ተላልፈው እንዲሰጡ ይህንን ሰይጣን እንደ ልዩነት ምክንያት ያሳያቸው ነበር፡- የአጵሎስ፣ የጳውሎስ፣ የኬፋ፣ የክርስቶስ በመባባል
·         በአሕዛብ መካከል በቁጥር ትንሽ ስለነበሩ እጅግ ይጨነቁ ነበር   2ቆሮ 2፥7
·         ጋብቻ መፈጸምና፣ ለጣዖት ያልተሰዋ ሥጋ ማግኘት እንኳን ከባድ ነበር::
v  መልዕክቱ የተጻፈበት ምክንያት:
1.   በቤተክርስቲያኒቱ ኃጢአትና ርኩሰት ዝሙት 1ቆሮ 5፥1 ፤ መለያየት  1ቆሮ 1፥11 ፤ መፈራረድ 1ቆሮ 6፥1 ፤ ለጌታ ክብር አለመሰጠት 1ቆሮ 11፥1 ስለበዛ ተግሳጽና ምክር ለመስጠት
2.   ሃይማኖታዊ ክርክሮችና ጥያቄዎች ስለበዙ መልስ ለመስጠት
·         ስለ ትንሳኤ ሙታን    1ቆሮ 15፥1 እስከ ፍጻሜው
·         ስለጌታ ራት    1ቆሮ 11፥1-16
·         ስለ ጋብቻ     1ቆሮ  7፥1 እስከ ፍጻሜው
·         በመንፈስ በጽድቅ ስለማደግ   1ቆሮ 3፥1-5
v  የመልዕክቱ ዋና ሐሳብ
·         በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተነሳውን ማዕበል ማቆም
·         ቅርጽ ያለው የቤተክርስቲያን አደረጃጀት መፍጠር
·         ቤተክርስቲያኒቱን ወደ ውበቷ መመለስ
·         አማኞችን ከአባልነት ወደ አካልነት ማሳደግ
·         ከእጮኝነትም አልፈው ለሚስትነት እንዲዘጋጁ ማድረግ
v  የመልዕክቱ ጸሐፊ  -    ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ
-          መንፈስ ቅዱስ
·         የጻፈው በኤፌሶን ተቀምጦ ሳለ  ከ55-56 ዓ. ም ባለው ነው።

Wednesday, July 31, 2013

የመጀመሪያይቱ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት በቆሮንቶስ ላለችው የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን


መቅድም
‘’የእግዚአብሔርን ኃይልና የቅዱሳት መጻሕፍትን እውነት አታውቁምና ትስታላችሁ’’ ማቴ 22፥29

                    ቅዱሳት መጻሕፍት በእግዚአብሔር ፈቃድ ለትምህርትና ለተግሳጽ ይሆኑ ዘንድ በተለያየ ጊዜ በመንፈስቅዱስ ምሪት በተለያዩ  የእግዚአብሔር ሰዎች ተጽፈዋል:: ዘመናትን የተሻገረና የሚሻገር የእግዚአብሔር ኃይልና እውነት በውስጣቸው ስላለ ሕያዋን ናቸው፡፡ አሁን ባለንበት ዘመንም ብዞዎችን ወደ ሕያው አምላክ እያደረሱ ይገኛሉ::
ሰው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረ ነው፡፡ እግዚአብሔር በባሕርዩ አዋቂ ነው፡፡ሰው ደግሞ  ለማወቅ ፣ ለመረዳት ዝግጁ የሆነ አእምሮ ተሰጥቶታል፡፡ ስለዚህ መማር፣መመርመርና ማገናዘብ ተፈጥሮአዊ ግዴታው ነው፡፡ ሆድ ምግብ እንደሚፈልግ አእምሮም ለእውቀት የሚሆነውን እውነተኛ መረጃ ይፈልጋል፡፡ስለዚህም ነው እግዚአብሄር በገነት ውስጥ ለአዳም ያስተማረውን የቃል ትምህርት ትውልድ በምድር ላይ እየበዛ ሲመጣ በመጽሐፍ እንዲሆን ያደረገው፡፡ ዘፍ 2፥1-ፍጻሜ

        ሰው ቅዱሳት መጻሕፍትን ማጥናትና መመርመር ካልቻለ እውነቱን ከሐሰት፣ቅድስናን ከርኩሰት፣ ዘላለማዊውን ከጊዜያዊ፣ ሰማያዊውን አስተሳሰብ ከምድራዊ እንዲሁም መንፈሳዊውን አኗኗር ከሥጋዊ መለየት አይችልም፡፡ጌታችን ኢየሱስ አይሁድን የነቀፋቸው የእግዚአብሔርን ኃይልና መጻሕፍት የያዙትን እውነት ባለማወቃቸው ነው፡፡  በተሰሎንቄ እና በቤርያ ከተማ በነበሩት ሰዎች መካከል ሰፊ ልዩነት የፈጠረው ማወቅ የሚፈልግ አእምሮአቸውን ተጠቅመው ቅዱሳት መጻሕፍትን የማጥናት/መመርመር/  እና ያለማጥናት ጉዳይ ነበር፡፡ ሐዋ 17፥1-13 ተክርስቲያን መንፈሳዊት ተቋም ናት፡፡ ስለዚህም በቅዱሳት መጻሕፍት  እውነት ላይ የተመሠረተ ጥልቅ መንፈሳዊነት ሊኖራት ይገባል:: መንፈሳዊነቷን ሊመጥን በሚችል መልኩም በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ መደበኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስተምህሮ መርሐ ግብር ሊኖራት ይገባል ፡፡እውነተኛው ሕግ፣ ታሪክ፣ ጥበብ የሚቀዳው ከዚሁ አስተምህሮ ነውና:: 

       የዱባይ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያንም በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተመሰረተውን የእግዚአብሔር ዕውቀት አማኞች ሁሉ እንዲያውቁና እግዚአብሔርን በማወቅ ወደሚገኝ እረፍት እንዲደርሱ ስትተጋ ሰንብታለች ትተጋለችም :: እስከ አሁን ድረስ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስተምህሮ መርሐ  ግብር ላይ እግዚአብሔር ጸጋውን ያበዛላቸው ብዙ መምህራን ተሳትፈዋል፡፡ ብዙውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም አስጠንተዋል፡፡እግዚአብሔር መሻትንም ማድረግንም ሰጥቶን  መጀመሪያይቱ የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች  መጽሐፍ ጥናት አሁን ባለንበት ወቅት በመምህር በሪሁን ወንድወሰን  ስናጠና ስንብተናል :: በነበሩን ጥናቶች ሁሉ ላይ ጸጋውን ያላጓደለ አገልግሎቱን በቅዱስ መንፈሱ ይመራና ይቆጣጠር የነበረ አምላክ ምስጋና ይድረሰው፡፡ለመምህራኑም  ጸጋውን ያብዛላቸው፡፡

      የቆሮንቶስ ምዕመናን ሕይወት አሁን እኛ ከምንኖርበት አኗኗር ጋር እጅግ የተነጻጸረ ከመሆኑም በላይ የዛሬዋ ዓለምና ርኩሰቶቿ በሚያስገርም ሁኔታ የዚያች ከተማ ግልባጭ እስኪመስሉ ድረስ አንድ ዓይነት ሆነዋል :: ቤተክርስቲያን ርኩሰት በበዛበት በዚህ ዓልም ውስጥ የምትገኝ መንፈሳዊ ተቋም እንደመሆኗ መጠን መንፈሳዊ ውበቷን ይዛ እንዴት መኖር እንዳለባት ስለመንፈሳዊና አስተዳደራዊ ውሳኔዎች፣ እንደ ሥጋ ወደሙና ትንሣኤ ሙታንን የመሰለ ጠንካራ መለኮታዊ ሀሳቦችን መንፈስ ቅዱስ አስተምሮናል::

    እያንዳንዱ ምዕራፍ በርዕስ ተከፋፍሎ ትምህርቱ መሰጠቱ አዲስ የአቀራረብ መንገድ የፈጠረ ሲሆን አጠቃላይ ጥናቱ በሚከተለው መንገድ ቀርቧል፡፡
  1. ሊቃውንት የዮሐንስ አፈወርቅ የአተረጓጎም ስልት የሚሉትን (መጽሐፍ ቅዱስን በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ሀሳብ መተርጎም) ተከትሏል፡፡
  2.  በሌሎች ክፍሎች ያሉ ተመሳሳይ ሀሳቦች እንዴት ሊገነዛዘቡና ሊጣመሩ እንደሚችሉ በምስጢራዊ ይዘትም ምን ያህል አንድነት እንዳላቸው ለማሳየት ተችሏል:: ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ  ሰዎች ቢጻፍምና በተለያየ ጊዜ ቢከተብም ሀሳቡ ግን የዘላለም እውነት እንደሆነ ለማስረዳት ተሞክሯል:: 
  3. በዚያውም  ምዕመናን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ለመዳሰስ እንዲሁም የማንበብ አድማስንና መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ልምድን እንዲያሳድጉ የተለየ መንገድን አሳይቷል፡:
       ይህንን ትምህርት ቤተክርስቲያናችን ለምዕመናኖቿ ካስተማረች በኋላ የተሻለ መንፈሳዊ ለውጥ ይኖራል ብዬ አምናለሁ:: መንፈስ ቅዱስ በብዙ ጸጋ ረድቶን ነበርና:: ይህ አገልግሎት በሚሰጥበት ጊዜ በልዩ ልዩ  መንገድ ያገለገላችሁትን ሁሉ የቤተክርስቲያን አምላክ በመንፈሳዊና በሥጋዊ በረከት መንፈሳዊና ሥጋዊ ኑሯችሁን ይሙላ::
እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅ አገልግሎቷን ያስፋ፡፡
ቀሲስ ተስፋ እንዳለ

የ ዱ/ቅ/ሚ/ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ አስተዳዳሪ

Monday, July 29, 2013

የሞት መድሀኒት

      እርሱ:-  ዘመናት ሳይፈጠሩ አስቀድሞ ለዘላለም ሃሳቡ አዘጋጀን፡፡ 
በሀጢያታችንም ሙታን ሳለን ወደደን፡፡ስለወደደንም መላዕክትን እንካን ሳይመስል እኛን መሰለ፡፡የጸጋ ሁሉ አምላክ ከአህያና ከላም ሙቀት ለመነ፡፡ በዚህም መዋረዳችንን ወስዶ ክብር አለበሰን፡፡አሁን ከእርሱ የተነሳ እንደ ባለ መዕለግ እንደ ባላማል ተቆጥረናል፡፡አሁን የምንተማመንበተ መርከብ ፤የምንደርስበት ወደብ አለን፡፡አባት አለን፡፡ልጆች ነን፡፡ወራሾች ነን፡፡ በሀጢያታችን የሚራራ ሊቀ ካህን አለን፤ከእስትንፋሳችን በላይ ቅርብ ነዉ ከመድህንና ከኢንሹራንስ ቀድሞ ይደርስልናል፡፡
ከምንምገዉ አየር በላይ ያስፈልገናል፡፡
በመስቀሉ ጥልን አስወግዶ በሞቱ ጠላት ገሎ
   በፋሲካዉ ሌሊት በዚያ ግሩም ሌሊት አጽድቆናል፡፡እናታችንም አባታችም እህታችንም ወንድማችንም ነዉ፡፡በምንም የማንመዘነዉ በማንም የማንቀይረዉ ዉዱ ገንዘባችነ ነዉ፡፡እናምነዋለን ከሕጻንነታችነን ዘመን ጀምሮ ጠብቆናለ ይህን ሁሉ ዘመን መግቦናል በብዙ በረከት አሳድጎናል ለኛ ያለዉ ገና ብዙ ነዉ፡፡
ይሄን ጌታ በምስጋና ላይ ምስጋና በቅኔ ላይ ቅኔ እየጨመርን እንዳበደ ሠዉ ዘመናችንን    ሙሉ ርቃናችንን ሆነን ብናገለግለዉ ያንስበታል እንጅ አይበዛበትም፡፡ይገባዋል፡፡          እርሱ ባለ    ዉለታችንነዉ፡፡                                                                              ስሙ ኢየሱስ ነዉ፡፡መድሐኒት::ያዉም የሞት መድሀኒት::

Thursday, July 25, 2013

ደመራ



                 

                         ደመራ

       ደመራ;- ደመረ ከሚለው መነሻ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም መሰብሰብ ማከማቸት እንደማለት ነው፡፡ ከዚህ ተነስተን ደመራ ማለት የመሰብሰብ ወይም የመደመር ሂደት (ደመራ፤ ድመራ ) ልንለው እንችላለን፡፡ 


        
ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሁሉም ከፈፀመ በኋላ እንደ ወንጀለኛ በእንጨት መስቀል ተሰቅሎ ሞተ ( መስቀል የወንጀለኛ መቅጫ ነበር) ጌታ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ የተሰቀለበትን መስቀል አይሁድ እንደ ተራ ነገር አውላላ ሜዳ ላይ ጣሉት ከጊዜ በኋላ ግን ወደ አይሁዳ ጆሮ አንዱ አንድ ነገር መጣ ፡፡ እንደ ቀልድ የጣሉት የክርስቶስ መስቀል ህሙማንን እየፈወሰ እውራንን እያበራ ድንቅ ታእምራትንም እያደረገ እንደሆነ ሰሙ፡፡ በዚህ ጊዜ ክርስቶስን ከከተማው አውጥተው እንደሰቀሉት ሁሉ መስቀሉንም እንዲሁ ከከተማ ውጭ አውጥተው በተራሮች መካከል ቀበሩት ቆሻሻም መጣያ አደረጉት፡፡


          እግዚያብሔር ግን ነገርን የሚያከናውንበት ጊዜ አለውና ደግሞ ዘመን መጣ፡፡ በእስጢፋኖስ ሞት የተበተነው የክርስትናው ዘር ማፍራት ጀመረ በሮም ነግሰው የነበሩት መክሲሚያኖስ እና ዲዮቅልጢያኖስ ክርስቲያኖችን እንደ ሰም እያቀለጡ እንደ ገል እያደቀቁ ከነፍሰጡሮች ማህፀን ሽል አውጥተው በሰይፋቸው እየሰነጠቁ በስቡ ጎራዲያቸውን በሚወለውሉበት በዚያ አስደንጋጭ የዘመነ ሰማዕታት የስቃይ ጊዜ ( በነገራችን ላይ ቤተክርስቲያን በዚያ ዘመን ከደረሰባት መከራ የበለጠ እስካሁን አልደረሰባትም ወደፊትም ይደርስባታል ተብሎ አይገመትም) ብዙ ክርስቲያኖች ዋሻ ውስጥ አበው ግበበምድር ይሉታል ገብተው ተውፊት ቁሳዊንና ትውፊት መንፈሳዊውን እየጠበቁ በብዙ መከራ የተስፋይቱን ቀን ሲናፍቁ ነበር፡፡
               በዚያ የክርስቲያኑ ስደት በተጀመረበት ጊዜ አንዲት ሴት ከነዚህ መከራ ከወረደባቸው ስለ ክርስቶስ መከራ የሚቀበሉት ጋር አብራ ገፈት ቀማሽ ነበረች ስሟ እሌኒ ይባላል፡፡ በኋላ የመከራው ዘመን ሲያልፍ ንጉስ ቆንስጣን አግብታ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ ወልዳለች፡፡ ንግስቲቱ እሌኒ በመከራ ውስጥ እግዚያብሔር የለያት ሴት፡፡
በንግስትነት ስትኖር ቤተመንግስቱ ስለተመቻት ክርስቶስን አረሳችውም፡፡ ይልቁንም የጌታ ፍቅር እንደ እግር እሳት ስለሚያንገበግባት እሱን በአይነ ስጋ ባገኘውም እንኳን መስቀሉን አግኝታ ገላው ያረፈበትን አቅፋ፣ ስማ ፍቅሯን ለማውጣት መንፈስ ቅዱስ አነቃት ወደ እየሩስ አሌምም መጣች፡፡
           የክርስቶስ መስቀል የተቀበረበት አካባቢ ማንም አያውቅም ያገኘችው አረጋዊ ሰው ኪሪያኮስ እንኳን አካባቢውን ከመገመት አባቶቻችን ከነዚያ ተራሮች በአንዱ ነው ይላሉ ከማለት የዘለለ ሊነግራት አልቻለም፡፡ ክርስቲያን ነገር ሲከብደው የሁሉ ነገር መፍትሔ ወዳለው ጌታ ይፀልያልና ንግስት እሌኒና አረጋዊ ክሪያኮስ ሱባዔ ይዘው ወደ ፈጣሪያቸው ማመልከት ጀመሩ፡፡
                በመንፈስ እንደተረዱት እንጨት ሰብስበው ደመራ ደምረው እሳት ሲያነዱ ከእሳቱ ላንቃ በላይ ተምዘግዛጊ ጢስ ወጣ ( ጢሰ ቅታሬ) እንደ ጦር ቀስት ምልክት ያለው፡፡
ጢሱም በአንድ ተራራ አናት ላይ ተተከለ፡፤ ሰው እግዚአብሔርን ማገልገል ሲያቅተው ግዕዛንና እንስሳት ያገለግሉታል ፡-የቢታንያ ዲንጋዮች ፣ የሰባ ሰገል ኮኮብ፣ የበልአም አህያ፣ የገሊላ ባህር አሁን ደግሞ የደመራው ጢስ በአይሁድ በላይ ባለአይብሮ ሆነ ጢሱም ያረፈበት ቦታ የመስቀሉ መገኛ መሆኑን ስላወቁ ደመራውን በደመሩበት ማግስት መስከረም 17 ቀን ቁፋሮ ተጀምሮ ቅዱሱ የጌታ መስቀል መጋቢት 10 ቀን ተገኘ፡፡
     እንዲሁም ሁሉም ሰው ሊረዳው የሚገባው ነገር እውነት በየትኛውም ተራራ ብትደፍን ቆሻሻም ቢከመርበት አንድ ቀን ንፁህ ሆና መውጣቷ የማይቀር መሆኑን ነው፡፡                  

          የእውነት አምላክ ይጠብቀን  ይሁን፡፡

Tuesday, July 23, 2013

ያልተቆረጠ ማንነት

    
                                                  ማር 1313-31

      ጌታ በምሳሌ ካስተማረባቸዉቀናት በአንዱ ከህጻንነቱ ጀምሮ የሙሴን ህግጋት የጠበቀ በነቢያት የተነገረዉን ሁሉ የሚፈጰም ሰዉ ወደ እርሱ ቀረበና የዘለዓለም ሕይወት እንድወረስ ምን ላድርግ ሲል ጠየቀዉ ASየዘለዓለም ሕይወት ማለት የማይቁረጥ ሕያዉነት ማለት ነዉ፡፡ ይህ ሕያዉነት ሶስት መልክ አለዉ፡-

1.      የእግዚአብሔር ሕያዉነት፡-ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የሆነ ሕየዉነት ነዉ፡፡ ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ የቁጥር መጀመረያ በሌለዉ ዘለዓለማዊነት አምላክነቱ አምላክነቱን እየባረከዉ በብርሃናዊነቱ ብርሃን በብርሃን ተከቦ ክብሩ ከብሩን እያወደሰዉ ቅድስናዉ እየቀደሰዉ ብቻዉን ይኖር ነበር፡፡ በዘመናትም መካከል ሕያዉ ነዉ፡፡ ከዚህም በኋላ ማለቂያ በሌለዉ የጊዜ ዑደት ከዘመናት ቁጥጥር ዉጭ በመሆን ዓመታትን እንደ ጨርቅ እያስረጃቸዉ ሕያዉ ሆኖ ይኖራል፡፡

2.     የመላእክት እና የሰዉ ሕያዉነት፡- አስቀድመዉ አልነበሩምና ከተፈጠሩበት ዕለት ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ሕያዋነ ነቸዉ፡፡
3.     የግዑዛንና የእንስሳት ሕያዉነት፡- አስቀድመዉ አልነበሩም ወደፊትም አይኖሩም ከተፈጠሩበት ጊዜ እስከ ሚጠፉበት (ሚሞቱበት) ጊዜ ሕያዋን ናቸዉ፡፡

የህግ ጠንቃቂ የዘለዓለምዊነት ጉዳይ ያሳሰበዉ ይመስላል ምክንየቱም ከሙታን ትንሳዔ በኋላም የሰዉ ሕያዉነት ይቀጥላል፡፡ ሰወችም ሕያዋን ሕያዋን ወይም ሕያዋን ሙታን ይሆናሉ፡፡ ማለትም በገሀነመ እሳት ወይም በመንግስተ ሰማያት የሚኖረዉ ይለያል፡፡ በተለይ ጌታ መንግስቱን በሕጻናት ምሳሌ ከሰበከ በኋላ በእግዚአብሔር መንግስት ዉስጥ ሕያዉ ሆኖ መኖር ሰወች የተፈጠሩበት ዋና ዓላማ እንደሆነ ገብቶታል፡፡ ነገር ግን ያንን የሕይወት መንገድ አላወቀዉም ከልጅነት ወራቱ ጀምሮ የጠበቃቸቸዉ ህግጋትም እርግጠኛ አላደረጉትም፡፡ለዚህም ነዉ ጌታ ከሙሴ ህግ ጠቅሶ፡-አትስረቅ ፤ አትግደል ፤ አታመንዝርሲለዉ እነዚህንማ ከልጅነቴ ጀምሮ ጠብቄያለሁ በማለት ከህግ በላይ የሆነ ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚወስድ አንድ መእገድ እያፈላለገ ያለዉ፡፡ አላስተዋለም እንጂ የዘለዓለም ሕይወት ከእርሱ ጋር እየተነጋገረ ያለዉ ነዉ፡፡
የቀደሙት የሰወች ሁሉ የሙሴን ህግና የቃልኪዳኑን ታቦት ትዕዛዝ ያለነቀፋ ጠብቀዉ ነበር ነገር ግን ህግ ፈረደባቸዉ እንጅ ለደህንነታቸዉ አልሆነም ፡፡ማንም ሰዉ ያለ እግዚአብሔር ምህርት ትምክህት የለዉም ከታላቁ አምላካችንና አባታችንና ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሳ እንጅ ህግጋትን በመፈጰም ማንም ወደዘለዓለም እረፍት አልደርስም፡፡ ጰጋዉ ካልረዳ በቀር ህግ በድካም እየፈረደ አንድስ እንካን የሚተርፍ አይኖርም፡፡እያንዳንዳችን ለህግ ቀጣት የሚሆን ማንነትና ድካም በዉስጣችእ አለ፡፡

       የሰዉየዉን ሁኔታ ስናጠናዉ ፍጹም ለመሆን የፈለገ ይመስላል፡፡ ጌታም ሀሳቡነ ወደደለትና ያለህን ለድሆች ሰጥተህ ተከተለኝ አለዉ (በሙሴ ህግ ራስህነን ትጠብቅ ነበር አሁን ለልሎች ትረፍ አለዉ) ሰዉየዉ ወደ ክርስትና ሊመጣ ነዉ ክርስትና ደግሞ ለልሎች መትረፍ ነዉ፡፡ ሰዉየዉ ግን አዝኖ ተመለሰ፡፡
ሰዉየዉ የሕይወት መረህ አልገባዉም ፤ ፍላጎት እንጅ ቁረጠኝነት የለዉም ፤ ስሜታዊም ነበር አሊያም እንደ ሕጰናት መሆን ማለት ጨዋታ መስሎታል፡፡በሕይወት እንቅስቃሴ ዉስጥ ሁሉም ነገር ዋጋ አለዉ ለማግኝት ማጣት ከፍ ለማለት ዝቅ ማለት ያስፈልጋል ሳይከፈል የሚወሰድ ነገር የለም፡፡ አስፈላጊ ለሆነ ነገር ዋጋ አለመክፈልም ራሱ የሚያስከፍለዉ ዋጋ አለ (not taking of a risk also risk )እንደሚሉት፡፡ የዘለዓለም ሕይወት ይፈልጋል ገንዘቡን ማጣት አይፈልግም ፤ እግዚአብሔርን ማምለክ ይፈልጋል ከሌላዉ አምላክ (ገንዘብ) ጋር አንደ ተጋባ ነዉ፡፡ልናሰታዉሰዉ የሚገባዉ ነገር ማንም መብቱን ለመጠቀም ሲያስብ ግጌታወቹን መወጣት የግድ መሆኑን ነዉ፡፡

         በሁለት ሀሳብ ማንከስ ለሁለት ጌታ መገዛት ጠፍንጎ የያዘን የጋራ ችግራችን ነዉ፡፡ (ተረት) አንድ ሰዉ ገደል ሊገባ ሲል አፋፉ ላይ ዛፍ አገኘና ተንጠለጠለ አመሰግኖ ሳያበቃ ዛፍዋ መወዛወዝ ጀመረች ጌታ ሆይ አድነኝ እያለ መጮሁን ተያያዘዉ ጌታም መጣና አድንሀለሁ የምታምነኝ ከሆነ ዛፍን ለቀቅዉ አለዉ ሰዉየዉ መላሶ አይ እግዚአብሔር አንተንም አምናለሁ ዛፍንም እይዛለሁ አለ፡፡ የመወሰን ችግር ፤ እርምጃ የመዉሰድ ችግር ፤ ነገን መፍራት ፤ ያለንበትነ ሁኔታ እነደ መቹ ማረፊያ መቁጠር ፤ ከመለኮታዊ ጥበቃ ይልቅ በዙሪያች ባሉ ሁኔታወች መደገፍ፤ባሮጌዉ እርሶ መቡካት ፤ በዱሮዉ ልምምድ መኖር ፤ ቀላቅሎ ለመኖር ምሞከር (መዝሙርም ጋር ዘፈንም ጋር ፤ ጣዖትም ጋር ታቦትም ጋር….) መዉጊያወቻችነን ናቸዉ ፡፡ መሀል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይመታልና አንዱን መቁረጥ ይገባል የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ፡፡ እነደዚህ አይነት የመንፈስ ዝለት እግዚአብሔርን በእግዚአብሔርነቱ መጠን ካለማምን የሚመነጭ ነዉ፡፡ይህ ደግሞ የክረስቶስ መልከ እንዳይኖረን ዉበታችንን እያጠፋ የጎሳቆለን አረም ነዉ፡፡ልንቆርጠዉ ይገባል እግዚአብሔር ያግዘን፡፡

       ወዳጆቸ፡- የማንወደውን እያደረግን የምንወደዉን ማድረግ ከተሳነን ሰነበትን፡፡ እስኪ በእግዚአብሔር ፊት እንሁን ለችግሮቻችን ሁሉመፍትሄ ያለዉ እርሱ ጋር ነዉ፡፡ይቆየን፡፡በመንፈስ ቅዱስ ሰለትነት ያረጀዉን ማንነት ይቁረጥልን አዲስ መንፈስና አዲስ ልብ ያድለን፡፡አሜን፡፡

ምስጋናና ዉዳሴ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ሕያዉ ለሆነዉ ይሁን፡፡አ ን፡፡፡፡፡