Wednesday, September 17, 2014

እግዚአብሔር የለምን?




  ከባለፈው የቀጠለ    ( መስከረም ሁለት ከሚለው ሃሳብ )
                            ማነው ቢሊኝ ማን ልበላቸው ???ዘጸ 3፤ 13-14
            ከሁለት ሰዎች የጀመረው የሰው ልጆች የትውልድ ሀረግ እግዚአብሔር እንዳለ  እየበዛና እየተባዛ ፤ እየረባና እየተራባ ምድርን መሙላት ጀመረ፡፡የሰው ልጅም ማንም ጣልቃ የማይገባበትን ነፃነቱን እየተጠቀመ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ ይሄድ ነበር ፡፡ ይህ ከሙሉ ነጻነት ጋር የተፈጠረ ትውልድ / የመጀመሪያው ትውልድ/ ምንም  እንኳን ከኤደን ገነት የተባረረ ስደተኛ ትውልድ ቢሆንም እስከ ኖህ ዘመን የጥፋት ውሃ መቅሰፍት ድረስ የዘመንና የእኗኗር ዘይቤ ልዩነት ቢኖርም እንኳን  ዛሬ ሰው የሚኖረውን አይነት ኑሮ እየኖረ ሰላማዊ ሕይወት ይመራ እንደነበር የቅዱሳት መጽሐፍት ምስክርነትና የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
           በዘመነ ኖህ ግን የእግዚአብሔርን የትዕግስት መጠን የተፈታተነው የዘመኑ ሰው ኀጢያት የቁጣ ጽዋው በሞላ ጊዜ ከኖህና ከቤተሰቦች በቀር ለወሬ ነጋሪ እንኳን ሳይቀር በንፍር ውሃ ተቀቅሎ ጠፉ፡፡ የመጀመሪያው ትውልድም ታሪክ ሆኖ ቀረ፡፡ አበቃለት፡፡ዘፍ 7፤1-ፍም
           ሁለተኛው ትውልድ እንግዲህ የጀመረው ከዚህ ቁጣ ካመለጡ  ስምንት ሰዎች ነው ፡፡/ ከኖህና ከቤተሰቡ/ ይኸኛውም ትውልድ ግን የባሰበትና የለየለት አመፀኛ ትውልድ ሆኖ አረፈው፡፡ በስነ መለኮት ሊቃውንትና በአይሁድ ታሪክ ጸሐፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ክርክር ያስነሳ ጉዳይ ቢሆንም የኖህ ልጅ ካም በአባቱ በኖህ ላይ እንኳን ሳይቀር ግብረ ሰዶም እስከ መፈፀም የደረሰበት ሁኔታ እንደነበር የሚያመለክቱ ሁኔታዎች አሉ፡፡ዘፍ 9፤20-24
            ከዚህም አልፈው ተርፈው ግንብ ገንብተው እግዚአብሔርን ጦርነት ለመግጠም ከጅለው ነበር ዘፍ 11፤1-9፡፡ የእግዚአብሔርም ቁጣ እየነደደ መጣ ነገር ግን በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች እግዚአብሔር በመጀመሪያው ትውልድ ላይ ያመጣውን መቅሰፍት በሁለተኛው ላይ አላደረገም፡፡
1.  ለኖህ ስለሰጠው ኪዳን ፡- የሰውን ልጅ ፈጽሞ ከምድረ ገፅ አላጠፋውም  ምልክት እንዲሆንህ ቀስቴን በደመና እሰውራለሁ የሚለውን ኪዳን ፤ ሰው ታማኝ ባይሆንም እንኳን እግዚአብሔር ግን ታማኝነቱ ሊያስቀር ኪዳኑን ሊተው አይችልም፡፡ ከዚህ የባሰ ቢያደርጉ እንኳን እርሱ ታማኝ እንደሆነ ይቀጥላል ፡፡ዘፍ 9፤13
2.   እግዚአብሔር አሁንም ሰዎችን ስለ ኃጢያታቸው ተቆጥቶ ቢያጠፋቸው እንደገናም ምድርን ቢሞሉ ተመልሰው መበደላቸውና መጥፋታቸው አይቀርም ፡፡ ስለዚህ የሰው ስራ እየበዙ እየበደለ መጥፋት የእግዚአብሔር ስራ የሰውን ኃጢያት እየተከታተለ ማጥፋት ሊሆን ነው ፡፡ ይህ ደግሞ መልካም አይደለም መቀጠልም የለበትም፡፡
ስለዚህ በነዚህና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የሰው ልጆችን ከጥፋት ለመታደግና ማንኛውም ሰው ተፈጥሮዊ ሞት እንዲሞት የጅምላ ሞት(ኣጠቃላይ መቅሰፍት እንዲቀር)እግዚአብሔር ሌላ መንገድ አዘጋጀ፡፡ ለራሱ የሆነ ትውልድ ከአህዛብ መካከል ለይቶ በስሙ ጠራ በኪዳን ምልክት የተለዩ አደረጋቸው ፡፡ ከቋንቋና ከነገድ ዋጅቶ ለዘለዓለም ድህነት መንገድ አድርጎ አዘጋጃአው፡፡     ይህንን ለመለኮታዊ ሀሳቡ እንዲሆን የፈለገውን ትውልድ የመምረጥ ሥራ አብርሃምን በመለየት ጀመረው ፡፡ዘፍ 12፤1 በአዲስ ምድርና አዲስ ተስፋ የራሱን ህዝብ ማዘጋጀት ጀመረ፡፡                                                                                                     በቁጥር ሰባ / 70/ በደረሱ ጊዜም ወደ ግብፅ ወሰደዳቸው፡፡ዘፍ 46፤8-27
               1ኛ. ከአህዛብ ምድር ፈፅመው እንዲርቁና ከባህሉና ከአምልኮው ፈጽመው እንዲለዩ፡፡
               2ኛ.የርሀብ ዘመን ስለ ነበር ህዝቡን ለማስመለጥ፡፡
               3ኛ.በግብፅ በሚጥማቸው መልካም ይሁን መጥፎ ነገር እግዚአብሔርን ማመን እንዲለማመዱ ሊቀርፃቸውና ሊያስተካክላቸው፡፡በዚህ የመከራ ዘመን በሚገጥማቸው እያንዳንዱ ነገር ውስጥ የእግዚአብሔርን ትድግና እያዩ ለዘላለም ልባቸው ሳይታወክ ለእግዚአብሔር መንግስት አገልግሎት የተለዪ ይሆኑ ዘንድ ነበር፡፡
ይኸ የእግዚአብሔር ልጆች የመጀመሪያ ስደት 450 ዓመት የፈጀ ነው፡፡ እስራኤልን እግዚአብሔር በሚፈልገው ቅርጽ ለመስራት 450 ዓመት አስፈልጎት ነበር፡፡ ይገርማል ፡፡

ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ የእግዚአብሔር ጊዜ ሲደርስ ለብዙ መቶ አመታት ሲያሰለጥነውና ሲያዘጋጀው የነበረውን ህዝቡ ይሰዋለትና ያመሰግነው ዘንድ ወዶ ወደ ተስፋይቱም ምድር ሊወስዳቸው ተነሳ ፡፡በፈርኦን ቤት አሳድጎ ሰማንያ አመት ያህል ያሰለጠነውን ታላቁን ነቢይ ሙሴን አስነሳው፡፡ እሳት የሚነድባት ነገር ግን የማትቃጠል ነበልባል አሳይቶ በድንቅ ተዓምር ለዘመቻው ይታጠቅ ዘንድ አመለከተው፡፡ (  ቁጥቋጦው በእሳት ያለመቃጠሉ ወይም ቁጥቋው እሳቱን ያለማጥፋቱ መለኮትና ሥጋ አንዱ አንዱን ሳያቃጥለው ተጠባብቀው ለመዋሃዳቸው ምሳሌ ነው ) ዘፍ 3፤1-12
እንዲህም አለው ሄደህ ለህዝቤ የአባቶቻችሁ አምላክ ልኮኛል በላቸው ነፃ የምትወጡበትና ወደ ርስታችሁ የምትመለሱበት ቀን እንደደረሰ ንገር አለው፡፡ ሙሴ ግን ማን ትባላለህ ማነው ቢሉኝ ማን ልበላቸው ብሎ ስለ እግዚአብሔር ህልውና ለማወቅ መሰረታዊ የሚባል ጥያቄ ጠየቀ ፡፡ እግዚአብሔርም የአባቶቻችሁ የአብርሃም፤ የይሳሃቅ፤ የያዕቆብ አምላክ ያለና የነበረ ያህዌ ነው ብለህ ንገራቸው አለው ፡፡ ያህዌ የሚለው የዕብራዊያን ቃል የግዕዙን እግዚአብሔር በቀጥታ ይተካል፡፡
እንግዲህ ከዚህ ጽንስ ሀሳብ ስንነሳ እግዚአብሔር ማለት ያለ፣ የነበረ ለዘለዓለም የሚኖር ማለት ነው ፡፡ እግዚአብሔር የሚለው ቃል ከሁለት ቃለት የተዋቀረ ነው፡፡ እግዚዕ ማለት ጌታ ማለት ሲሆን ብሔር  ማለት ደግሞ ህዝብ፣ ሀገር  እንደ ማለት ነው ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ማለት የለና የነበረ ለዘለዓለም የሚኖር የህዝብ ሁሉ ጌታ፣የሀገር(የዓለም) ሁሉ ገዥ  የሚል ትርጉም ይሰጠናል፡፡
·         እኛ እግዚአብሔር የሚለውን ስም ስንጠራ ( ስላሴን ) አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስን እንደሚወክልልን ግንዛቤ በመውሰድ ነው ፡፡ ሊቃውንት የስሙን ትንታኔ እንዲህ ያስረዳሉ
             እግዚዕ   -   ጌታ   - ኢየሱስ - ወልድ
             አብ -        አባት  - አባት -    አብ
             ሔር -       ቸር   - አጽናኝ -መንፈስ ቅዱስ
እግዚአብሔር              አብ፣ ወልድ ፣ መንፈስ ቅዱስ
           እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለውን ስም በተረዳነው መንገድ እንዲህ ከተነተነው በእርግጥ እግዚአብሔር አለ ወይ? አለ ያልነው አለ ብለው ስለነገሩን ወይስ የሃይማኖት፣ የታሪክ ፣የሳይንስ… ማረጋገጫዎች አሉን ? የሚሉት ጥያቄዎች በግድ መመለስ አለባቸው ፡፡
          የእግዚአብሔርን ህልውና በተመለከተ አጋንንት እንኳን ሳይቀሩ የሚመሰክሩት ሀቅ ነው ፡፡ ልዩነቱ በአማኞች ዘንድ ያለው እግዚአብሔር ማወቅ በመታዘዝና በመገዛት፤ በማምለክና በማመን የሚገለጽ መሆኑ ነው ፡፡ የዘመናችን ፍላስፎችና የእውቀትን ጥግ የነኩ ሳይንቲስቶች ሳይቀሩ ወደ ሕይወታቸው መጨረሻ ሲቃረቡ አንድ  ኃይል አለ ብለው ማመናቸው እየተለመደ ያለ ጉዳይ ነው ፡፡ ይሁን እንጅ  ሀልወተ እግዚአብሐየርን  ለማረጋገጥ የትኛውም ፍጡር ውስንነት አለበት፡፡የእግዚአብሔርን ህልዉና በምልአት የሚያረጋግጠው ራሱ እግዘአብሔር ነው ፡፡ነገር ግን  አንዳንድ አስረጅዎችን ብንጠቅስ የበለጠ በእግዚአብሔር ህልውና ላይ ያለንን እውቀትና  እምነት ያሳድግልናል፡፡
1.  ተፈጥሮ ፡- እግዚአብሔር ለፍጥረቱ በፍጥረቱ ይታወቃል፡፡ ስነ-ፍጥረትን ሁሉ ጠይቅ ማን እንደፈጠራቸው ይነግሩሃል ሮሜ 1፤20-21 የተሰራ ሰሪውን ይገልጣል ( የማን ልጅ፣ የማን ቤት )እንደሆነ
          የሰማዪ ትልቅነት ያስደንቃል፣ የምድር ስፋት ወሰን ዳርቻ የለውም ፣ በሰማይ ደረት ላይ እንደ እንቁ ፈርጥ የተለጠፉ ከዋክብት ያስደንቃሉ፣ ታላቁ የባህር ማዕበል በውቅያኖሱ ደረት ላይ ፈረሰኛ ይጋልባል በቃ ተፈጥሮ ትልቅነቱ፣ ግዝፈቱ፣ ርቀቱ፣ ብዛቱ፣ጥልቀቱ፣ … ብዙ ብዙ ነረጉ ይገርማል ፡፡ ይህንን በምትሃት ወይም በአስማት ተገኘ ብሎ ማሰብ እብደት ነው ፡፡ እነዚህን ያስገኘ መኖር አለበት፡፡መኖሩ ብቻ አይደለም እነዚህን ሁሉ ፈጥሮ በየስማቸው እየጠራ ማወቁ፣ ደግሞም መመገቡና መጠበቁ፣ ከዚህ ሁሉ በላይ  ሃያ ሁለቱን ስነ-ፍጥረታት ሃያውን ዓለማት  በእቹ የያዘ መሆኑ ይደንቃል፡፡አዎ ምን ያክል ይሆን እሱ፤- ቁመቱ፣ ርዝመቱ፣ ችሎታው … እነዚህን ሁሉ ግዙፍ ግዑዛንና ህያዋን እንዴት በእጁ ያዛቸው በእርግጥ እርሱ ታላቅ ነው ፡፡
         የማይወሰን ፣ ሁሉን አዋቂ ፣ በሁሉ ቦታ የሚገኝ ፡፡ብቻውን ንጉስ የሆነ ህዝብና ሀገር ሳያስፈልገው በባህርይው የነገሰ፡፡  ያለና የነበረ ከዘላለም እስከ ዘለዓለም ህያው የሆነ፤ የመኖሪያ መንገዶች ሁሉ አዲሽ፤ የተሰበሩ አጥንቶችን ሁሉ የሚጠግን፤ የጥልቀቱን መሠረት በንፋስ  አስሮ ከሰደማያት በላይ ክብሩን የዘረጋ ፤መጎናፀፊያውን ከመብረቅ ጫማውን  ከነበልባል ቀሚሱን ከእሳት የሰራ ፤በሚያምኑት ልብ በክብር የተቀመጠ አባትና አምላክ እርሱ እግዚአብሔር ነው ፡፡  
2.  የስነ -ፍጥረት አኗኗር፡- ማንኛውም  አይነት አኗኗር የራሱ የሆነ ዘይቤ ፣ ህግና ወሰን አለው ፤ በማህበራዊ ህይወት እንኳን ህግና ፖሊስ ባይኖር ኖሮ ሰይጣን ይጨርሰን ነበር፡፡ መጠበቅ ያለባቸው የባህል ፣ የማህበረሰብ ፣ የሀገር ውርሶች አሉና እነዚህን መጠበቅ ካለተቻለ አንድ ህዝብ እንደ ህዝብ ም እንደ ሀገርም መቀጠል ያዳግተዋል ፡፡
         ተፈጥሮም እንዲሁ ነው ፤ የሚጠብቀው፣ የሚቆጣጠረው ህያው የሚያረገውና የሚያሳልፈው ያስፈልገዋል ፡፡ ባይኖር እንኳን የግድ መኖር አለበት  ፡፡እስኪ ተፈጥሮን ተመልከቱ ከመሬት ስር ያለው ውሃ  ነው( አፈር ውሃ ላይ ቆሞዋል ማለት ነው ነገር ግን ውሃው አፈሩን አቅልጦ መሬት አልጠፋችም ) ከውሃው አልፈን ወደ ውስጥ ቆፍረን ከገባን እሳተ ገሞራ አናገኛለን እሳቱም በውሃው አልጠፋም፤ ከእሳቱ ስር ነፋስ አለ ነፋሱም እሳቱን አግለብልቦ ዓለም አላቃጠላትም ሁሉም ተጠባብቀው አንዱ አንዱን ሳያጠፋቸው ይኖራሉ፡፡ ተጠባብቀው እንዲኖሩ ግን ተቆጣጣሪ ጠባቂ ያስፈልጋል ፡፡
          መሬት በፀሐይ ዙሪያ ስትዞር አሁን ካለችበት ወደ ፀሐይ ትንሽ ጠጋ ብትል መሬት ትቀልጣለች፤ መሬትና ፀሐይ በራሳቸው ርቀት እንዲቀጥሉ መሬትም ምህዋርዋን እንዳትለቅ ለብዙ ሺህ ዘመን የጠበቀ ለዘላለም ሳያንቀላፋ የሚጠብቅ አለ ፡፡ ክረምትና በጋን በወቅቱ የሚያፈራርቅ፣ እፅዋት በካርቦንዳይ ኦክሳይድ፣ ሰዎች በኦክስጂን  እንዲተነፍሱ አንዱን ለአንዱ አስፈላጊ አድርጎ የፈጠረ ይህም ሂደት እንዲቀጥል ያደረገ አለ ፡፡ ስንተኛ የት እንደምንሄድ ባይታወቅም የሄድንባት ሄደን ስንመለስ በህይወት እንድንኖር የሚያደርግ ፤እኛ አንቀላፍተን ሳለ የማያንቀላፋ የስነ ፍጥረት አኗኗር ያለ ችግር ደረጃውን ጠብቆ ሒደቱ ሳይዛነፍ ቀጣይ እንዲሆን ያደረገ አለ፤ እርሱ እግዚአብሔር ነው ፡፡ እንዲህ ባይሆን ኑሮ አቶሚክና ኒውክለር ያላቸው ብዙ ኃያላን ዓለምን በፈለጉ ጊዜ ማኖር በፈለጉ ጊዜ ማጥፋት በቻሉ ነበር ፡፡
3.          ህሊና፡- ህሊና ትንሹ እግዚአብሔር  ነው ፡፡ እውነተኛ ምስክርም ነው፡፡ አምባገነኑ የራሽያ ሶሻሊስት መሪ ሚካኤል ጎርባቾቭ ስብሰባ በመራ ቁጥር እግዚአብሔር የለም ይል ነበር እናም በዘመኑ የነበረ አንድ ጋዜጠኛ ለምን ሁል ጊዜ እንዲህ እንሚል ቢጠይቀው ህሊናየ አለ እያለ እያስቸገረኝ ነው አለ ፡፡ እውነት ነው ህሊና የእግዚአብሔርን ህልውና ማረጋገጫ ነው ፡፡ መጥፎውን መጥፎ ይላል ለማንም ኣዳላም ለማንም አይወግንም፡፡መጥፎውን መጠጥፍ መለካሙ መልካም እነዲል ግን የሚመሰክርለት ያስፈልገዋ ያ ለህሊና የሚመሰከርለት ከሀሳባችንና ከአዕምሮዎችን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው መንፈስ የሆነ አካል እግዚኣብሔር ነው፡፡
4.          የህሊና ዝንባሌ ፡- ሰው እንዲሁ አምላክ ናፋቂ፣ ረዳት ፈላጊ ፣ ውሱንነት ያለበት ፍጥረት ነው ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በሚያገለግልበት ዘመን የግሪክ ሰዎች ለማይታወቅ አምላክ ብለው በሰሩት ቤተ መቅደስ መካከል አንድ ክፍል ትተው ነበር፤ ጳውሎስም ይህንን የህሊናቸውን ዝንባሌ ተመልክቶ የማይታወቅ ስላሉት ነገር ግን ስለሚታወቀው አምላክ ሰበከላቸው ፡፡ አዳም ከእግዚአብሔር ከተጣላበት ጊዜ ጀምሮ አምላክን በከፍተኛ ሰቀቀን ሲናፍቅ ኖሯል ፡፡ ሰው የተሰራበት ስነ- ተፈጥሮ አምላክን ስለ ሚመስል አምላክን የመናፈቅና ወደ ፈጣሪው የመጠጋት ዝንባሌ አለው ፡፡
         ለምሳሌ ፡- አንድ እግዚአብሔር የለም የሚል ሰው ቢኖር ነገር ግን በጣም የሚያስጨንቅ ነገር ቢገጥመ እግዚአብሔር የለም እያለ  እንኳን  በውስጡ ኧረ አምላኬ ተው እርዳኝ ማለቱ አይቀርም ህሊናው ወደ እግዚአብሔር ያዘነብልበታል ወይም በተቃራኒው በጣም የሚያስደስት ነገር ቢገጥመው በደስታ ስሜት  እየተፍለቀለቀ ለሆነ ኃይል ሳያስበው ምስጋና ሲያቀርብ ተመስገን ሲል ራሱን ያገኘዋል ያ የሚያመሰግነው ርዳታ የጠየቀው እርሱ እግዚአብሔር ነው ፡፡
5.        ታሪክ ፡- ሳይንስ ፣ አርኪኦሎጂ፣መጽሐፍት፤- እነዚህ በተለይ ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔርን ህልውና ለመረዳት መስታዊ ናቸው ፡፡ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ የተከናወኑትን ነገሮች ስንመረምር ሰው ያከናወናቸውና ደግሞ ያላከናወናቸው ብዙ ነገሮች አሉ በዚህ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በረቀቀበት ዘመን አንኳን ሰው ማድረግ ያልቻላቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ስላልተከናወኑት ነገሮች ስናስብ ከሰው አቅም በላይ የሆኑ ነገሮች ስላሉ የተሻለ አቅም ያለውን እንድንፈል ያስገድደናል፡፡ ተከናወኑ የምንላቸው ነገሮች ፍጹምነት የሌላቸው መሆኑ በራሱ የስልጣኔን እንክን ያጎላዋል ስለዚህም ሌላ ፍጹም የሆነ እንድንፈልድ እንገደዳለን ፤፤በተቃራነኒው ደግሞ እግዚአብሔር በሚባለው አምላክ የሚያምኑ ከዘመኑ ስልጣኔ አቅም በላይ የሆኑ እጅግ አስቸጋሪ ነገሮችን ሲያከናውኑ፣ ሲፈውሱ የሞተ እንኳን ሲያስነሱ እናያለን ፡፡ ስለዚህ በዘመን ሁሉ ይህንን ካየን ከተፈጥሮ በላይ ከስልጣኔ በላይ ፣ ከእውቀት በላይ የሆነ እንዳለ የዓለም የራሷ አቀመ ቢስነት ያስገነዝበናል፡፡ የብዙ ሊቃውንት ምስክርነት፤ የአርኪኦሎጅ ቅሪቶች ፤የታሪክ ድርሳናትና ቅዱሳት መጽሐፍት ይህንኑ ሀቅ ያስረዳሉ፡፡
6.         ኢየሱስ ክርስቶስ ፡- እግዚአብሔርን ያየው ማንም የለም በአባቱ እቅፍ ያለ አንድያ ልጁ ተረከው እንጂ ዮሐ 1፤18  እግዚአብሔር መንፈስ ነው የሚመለከውም የሚሰገድለትም በመንፈስ ነው ፡፡ እርሱንም አይቶ በህይወት የሚኖረው ማንም አይኖርም ፡፡ ነገር ግን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሥጋ በለበሰ ጊዜ እግዚአብሔርን በክርስቶስ በኩል አየነው፡፡በዚህም ምክንያት ስለ እግዚአብሔር ያለን እውቀት ወደ ፍጹምነት አደገ ስላሴን አየን፡፡ አብ፣ወልድ፣መንፈስ ቅዱስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ገባን፡፡ በረጁሙ ተራራ ላይ በግርማው በታየ ጊዜ የምወደው ልጀን ስሙት ብሎ አባት ሲመሰክር በእርግጥ አብን አየን በተጠመቀበት ባህር አናት ላይ መንፈስ ቅዱስ የርግብ አምሳል ሆኖ ዮርዳኖስን ሲሸፍነው መንፈስ ቅዱስን ደግሞ አየነው ወልድ ደግሞ በድንቆችና በትአምራት በመዋዕለ ሥጋዌው በህዝቡ መካከል ያልፍ ነበር ፡፡ አብና መንፈስ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመመስከር በተገለጡ ጊዜ ሥላሴ ብለን ያመነውም በእርግጥ እውነት እንደሆነ ተረዳን ፡፡
       ክርስትና የመገለጥ ሃይማኖት ነው፡፡ አብ ፣ ወልድ ፣ መንፈስ ቅዱስ የተገለጡበት እና አንድ እግዚአብሔር ብለን ያመንበት ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የተረከልን፤ የሰውና የእግዚአብሔር ወኪል ሆኖም በተዋህዶ አካል ያስታረቀን፡፡እንደውም  እግዚአብሔርን የበለጠ እንድናውቀው የሆነበት ይህ መገለጥ ባይኖር ኖሮ እግዚአብሔርን ብናውቀውም እንኳን በዚህ መጠን ባላወቅነው ነበር ፡፡አሁን ግን ከዚህ ታላቅ መገለጥ የተነሳ ወደ ተሻለ መርዳት ደርሰናል ፡፡1ኛ ዮሐ 3፤4-8 ማቴ 17፤1 ማቴ 4፤1
      እግዚአብሔርን ህልውና ማወቅ ከአጋንንት እውቀት ፤ ዋጋ ከሌለው እውቀት ወይም ሞት ከሚያመጣ እየእግዚአብሔርውቀት የተለየ ህይወትን የሚሰጥ እውቀት ነው ፡፡ ከዚህ ሁሉ የበለጠ በእግዚአብሔር መታወቅ ደግሞ እጅግ ታላቅ ነው ፡፡
                                  በዘለዓለም አምላክእግዚአብሔር   የታወቅንእንሁን  ፡፡                                               እግዚአብሔር ያግዘን ፡፡




3 comments:

  1. መምህር ቃለህይወት ያሰማልን። ነገር ግን ጥያቄ አለኝ። ካም በአባቱ ላይ ግብረሰዶም እንደፈፀመ መረጃውን ሰፋ አድርገህ ብትገልፅልኝ። ምክንያቱም በዘፍ 9:20 ጀምሮ ስለዚህ ጉዳይ አይገልፅም።

    ReplyDelete
  2. ትክክል ዘፍ 9:20 ስለ ግብረስዶም አይገልፅም ለምን ይህን ቃል
    እንድተጠቀሙ አልገባኝም፡፡

    ReplyDelete
  3. የመምህር በሪሁን ገጽ: እግዚአብሔር የለምን? >>>>> Download Now

    >>>>> Download Full

    የመምህር በሪሁን ገጽ: እግዚአብሔር የለምን? >>>>> Download LINK

    >>>>> Download Now

    የመምህር በሪሁን ገጽ: እግዚአብሔር የለምን? >>>>> Download Full

    >>>>> Download LINK

    ReplyDelete